April 2, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በቻይና የተሰራው የዓለማችን ግዙፉ የጭነት ድሮን


ቻይና በሰው-አልባ የጭነት አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የ3.5 ቶን ጭነት የመሸከም አቅም ያለውን ግዙፍ ድሮን የበረራ ሙከራ በስኬት ማጠናቀቋን አስታውቃለች።

‘ቻንግዪንግ-8’ የተሰኘውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ይህ ድሮን፣ ሞተሩን ጨምሮ ሁሉም አካላቱ በቻይና የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅም ብቻ የበለጸጉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲሲቲቪ እንደዘገበው፣ የድሮኑ የበረራ ሙከራ በሄናን ግዛት ዠንግዡ አውሮፕላን ማረፊያ የተከናወነ ሲሆን፣ ድሮኑ በማኮብኮቢያው ላይ 280 ሜትር ብቻ ከተጓዘ በኋላ ለ30 ደቂቃ ያህል በአየር ላይ በረራ አድርጎ በሰላም ማረፉን ገልጿል።

ይህ ስኬት ቻይና በ7 ቶን ክብደት ክፍል ውስጥ የሚመደቡ ዘመናዊ ሰው-አልባ የመጓጓዣ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ረገድ ትልቅ እመርታ ማሳየቷን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

በበረራ ሙከራው ወቅት የድሮኑ ዘመናዊ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ሜካኒካል ክፍሎች፣ የኃይልና የነዳጅ ሥርዓቶች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በዝርዝር ፍተሻ እንደተደረገለት ተጠቅሷል።

ድሮኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲሰማራ፣ በፊቱና በኋለኛው በኩል በተገጠሙ በሮች አማካኝነት 3.5 ቶን የሚመዝን ጭነትን በ15 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ጭኖ ወደ መዳረሻው ለማድረስ ያስችላልም ነው የተባለው።

EBC