የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን ቅደም ተከተል ለመወሠን የሚያስችለውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ መጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ አስጀመረ።
የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና የመገናኛ ብዙኃን አካላት የተገኙበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ ያከናወናቸውን ተግባራት በዝርዝር አስረድተዋል።
የፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን የአደራደር ቅደም ተከተል አስመልክቶ ሲናገሩም፤ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት የሚከናወነው በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች ምሥልና የመለያ ምልክት አቀማመጥን የሚወሥነው የዕጣ ማውጣት ሂደት መጠናቀቅን ተከትሎ እንደሆነ ተናግረው።
በዚኽ ሂደት ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮቻቸው እንዲገኙ በማድረግ ሂደቱን እንዲከታተሉ፤ ሂደቱ የማይቋረጥ በመሆኑም ተወካይ ያልላከ ፓርቲ ቢኖር የሌሎች ፓርቲዎች ተወካዮች ባሉበት የተካሄደውን ዕጣ ማውጣት ውጤት ለፓርቲው የማሳወቅ ሥራ ቦርዱ እንደሚሠራ አሳውቀዋል።
የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የሕግ ባለሞያ የሆኑት አይተነው ደበበ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች አደራደር ዕጣ አወጣጥ መመሪያን ዝርዝር ድንጋጌዎች ያስረዱ ሲሆን፤ የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓትን ለማካሄድ የለማውን ሲስተም በተመለከተ ደግሞ የቦርዱ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ማስተባበሪያ ሥራ ክፍል ኃላፊዋ ቀነኒ እንሰርሙ ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የምርጫ፤ የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 37(7) ላይ ቦርዱ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች ምሥልና የመለያ ምልክቶችን አቀማመጥ፣ ቅደም ተከተልና እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ግልጽ በሆነ መንገድ በመመሪያ እንደሚወሥን ይደነግጋል ሲል ቦርዱ በይፋዊ ገጹ አሳውቋል
More Stories
በኢራን ጉዳይ ቻይና ጥሪ አቀረበች
ትራምፕ በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ ወደ አምስት ቀናት አራዘሙ
የትራምፕ የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ እና የኢራን ምላሽ