የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ ዳግም የማትከፍት ከሆነ የሀገሪቱን የሃይል ማመንጫ ማዕከላት እንደሚያወድሙ አስጠንቅቀዋል፡፡
ኢራን በበኩሏ ለሚፈጸምባት ጥቃት በቀጣናው በሚገኙና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው የሃይል ማመንጫ ማዕከላት ላይ አስፈላጊውን አጸፋዊ ርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡
አራት ሳምንታትን ያስቆጠረው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል፡፡
በተለይም ጦርነቱን ተከትሎ ወሳኝ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ መስመር የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን መዘጋት ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡
በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ሳቢያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን÷ ይህም የበርካታ ሀገራት ኢኮኖሚ ብርቱ ፈተና እንዲገጥመው አድርጓል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ ዳግም ሙሉ በሙሉ የማትከፍት ከሆነ ከባድ ጥቃት እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ቴህራን እስከ መጋቢት 23 እኩለ ሌሊት ድረስ መስመሩን የማትከፍት ከሆነ አሜሪካ በሀገሪቱ የሃይል ማመንጫ ማዕከላት ላይ ጥቃት በመፈጸም ሙሉ በሙሉ ታወድማለች ነው ያሉት፡፡
ኢራን ለፕሬዚዳንቱ ማስጠንቀቂያ በሰጠችው ምላሽ÷ በቴህራን የነዳጅ ማምረቻ ማዕከላት ላይ ለሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ተመጣጣኝ አጸፋዊ ርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
አሜሪካ ጥቃቱን የምትፈጽም ከሆነ በቀጣናው የሚገኙ የዋሽንግተን የሃይል፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደምትፈጽም ማስገንዘቧን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በቀጣናው ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል፡፡
በጦርነቱ ለሕልፈት ከሚዳረጉት በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸው የወደመባቸው ዜጎች ለአስከፊ ችግር መዳረጋቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡
More Stories
እንግሊዝን ያስቆጣው የኢራን ጥቃት
በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐግብር የተሠማሩ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣቸው ተገለጸ።
ኢራን ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ወታደራዊ ዘመቻ …