March 21, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐግብር የተሠማሩ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣቸው ተገለጸ።

በዘርፉ የተሠማሩ ወጣቶች በወተት እና እንቁላል አቅርቦት የቴፒ ከተማ ገበያን እያረጋጉ ስለመሆኑ የከተማው ግብርናና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።

የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ወደ ተግባር ከገባ ወዲህ በዘርፉ የተሠማሩ ወጣቶች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱን በወተት ላም፣ በእንቁላል አቅርቦት እና በመኖ ማቀነባበር ዘርፍ የተሠማሩ ወጣቶች ገልጸዋል።

በቴፒ ከተማ ህብረት ቀበሌ በወተት ላም እርባታ ከተሠማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት አያሌው ሕይወቴ በአሁኑ ሰዓት 10 የሚታለቡ ላሞችና ሌሎች ላሞችን በመያዝ ለከተማው በተመጣጣኝ ዋጋ ወተት አያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቂ ወተት እያቀረበ መሆኑን ጠቅሶ ወጣቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥ አስገንዝቧል።

በተለይ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት የሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል ለተጠቃሚነታቸው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሶ ወጣቱ በዘርፉ በመሠማራት ከሰው እጅ ማየት መላቀቅ እንዳለበትም አሳስቧል።

ከማህበሩ ወተት ከሚጠቀሙ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ወንድወሰን መንግሥቱ የሌማት ትሩፋት ለአካባቢው ህዝብ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሷል።

ይህም የከተማውን ነዋሪ የወተት እና የእንቁላል ፍላጎት ከማሟላቱም ባሻገር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ መሆኑና ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ሲል ጠቅሷል።

ዘርፉን አስፍቶ ማስቀጠል እንደሚገባም ወጣት ወንድወሰን ጥሪ አቅርቧል።

በመኖ ማቀነባበር ዘርፍ ከተሠማሩ ወጣቶች መካከል የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ተመስገን ዘለቀ በበኩሉ ለ10 ሆነው መደራጀታቸውን ጠቅሶ በዘርፉም ከራስ አልፈው ለሌሎች ወጣቶች የተረፈ ተግባር ለመከወን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጿል።

ዘርፉ አዋጭ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ተመስገን የመኖ ማቀነባበሪያው በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር ሲገባ በሰዓት እስከ 30 ኩንታል መኖ የማቀነባበር አቅም እንዳለውም ገልጿል።

ይህም ማህበሩ ከዞኑ አልፎ ለአጎራባች ዞኖችና ክልሎች መኖ የማቅረብ አቅም እንደሚፈጥር የጠቆመው ወጣቱ ነጌን የተሻለ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ተናግሯል።

ሌሎች ወጣቶችም የእኛን ፈለግ በመከተል ከራስ አልፈው ለሀገር ብልፅግና እንዲተጉ ስልም ወጣት ተመስገን መልዕክት አስተላልፏል።

በቴፒ ከተማ በተሰራው የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ከአራት በላይ የወተት እና አራት የእንቁላል መንደር እንዲሁም በሌሎችም መሰል ዘርፎች ወጣቶችን በማደራጀት አበረታች ውጤት መመልከት መቻሉን የቴፒ ከተማ ግብርናና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አለማየሁ ገልጸዋል።

በዚህም ከአንድ የወተት ማህበር እስከ 150 ሊትር ወተት እና ከአንድ የእንቁላል አቅራቢ ማህበር እስከ 8 መቶ እንቁላል በቀን ለከተማው ማቅረብ እየተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ በመሆኑ በገበያው ላይ እፎይታ ከመፍጠሩም ባሻገር የማያቋርጥ አቅርቦት እንዲኖር ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በመኖ አቅርቦት ረገድም የወጣቶች ተግባር እንዳይስተጓጎል የክልል፣ የዞንና የቴፒ ከተማ አስተዳደር በመተባበር በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በመትከል ተያያዥነት ያለውን ስራ ዕድል ለወጣቶች መፍጠር መቻሉን አቶ አየለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በእያንዳንዱ የወተት መንደር እስከ 25 የሚሆኑ የተዳቀሉ ዘመናዊ ላሞችን የያዙ ሼዶች ይገኛሉ ያሉት አቶ አየለ ዘርፉን አስፍቶ ለማስቀጠል ሌሎች ሼዶችን ከማስገንባት ባሻገር ከኦሞ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ስራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ስራ አጥ ወጣቶች ዘርፉን በመምረጥና ወደ ተግባሩ በመሰማራት ዕድሉን መጠቀም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

#SWMN