March 19, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለ1,447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1,447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ። ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢድ አልፈጥር በዓል የትዕግስት፣ የመስዋዕትነት፣ የርኅራኄ እና የአንድነት እሴቶች የሚጎሉበት ልዩ ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም በታላቁ የረመዳን ወር የእምነቱ ተከታዮች ሲያሳዩት የነበረው ጾም፣ ጸሎትና ለተቸገሩ ወገኖች የሚደረግ ርኅራኄ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምና መተሳሰብ እንዲሰፍን የላቀ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል ።

ክልሉ የበርካታ ብሔረሰቦች፣ እምነቶችና ባህሎች መገኛ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በተለያዩ እምነቶችና ባህሎች ውስጥ ቢንኖርም፣ በአንድነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ መኖር የቆየና የጸና ባህላችን ነው ብለዋል። ይህንን የቆየ ማህበራዊ እሴት ይበልጥ በማጎልበት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በበዓሉ ወቅት ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ለድሆችና ለችግረኞች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያነሱት ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ፣ ይህም ለዜጎች አንድነት መጠናከር የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሌሎች እምነት ተከታዮች ከእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር የበዓሉን ደስታ በመጋራት፣ በፍቅርና በክብር ያላቸውን አጋርነት እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም 1,447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ለሁሉም ዜጎች የሰላም፣ የፍቅር፣ የተስፋ እና የበረከት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።