March 9, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ድሮኖች አረምን ለመከላከል እየረዱ ነው፡፡

ማሻ፤ የካቲት 30/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በእንግሊዝ የሚገኘው የሮያል ግብርና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አርሶ አደሮች አረምን በዘመናዊ መንገድ የሚከላከሉበትን ቴክኖሎጂ ይፋ አደረጉ።

ይህ ቴክኖሎጂ ድሮኖችን እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም በእርሻ ማሳ ውስጥ የሚገኙ አረሞችን በትክክል ለይቶ ለማወቅ ያስችላል። ይህም የኬሚካል አጠቃቀምን በመቀነስ መድኃኒት በሙሉ ማሳ ላይ ከመርጨት ይልቅ አረም ባለበት ቦታ ላይ ብቻ እንዲያርፍ ያደርጋል።

ይህ ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሮች አስቸጋሪ እና ረጅም ጊዜ የሚወስደውን አረምን የመከላከል ስራ በአጭር ጊዜ ያከናውናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እንዳስታወቁት በዚህ ቴክኖሎጂ አረሞች የሚገኙበትን ቦታ በትክክል መለየት ይቻላል። ይህም ለጠቅላላው እርሻ ፀረ-ተባይ ወይም ፀረ-አረም ከመጠቀም ይልቅ ለሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ብቻ ለመጠቀም ያስችላል፡፡

ቴክኖሎጂው ወደ አፈርና ውሃ የሚቀላቀሉ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በመቀነስ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቁ በተጨማሪ አነስተኛ ኬሚካል ጥቅም ላይ በማዋል የአርሶ አደሩን የምርት ወጪ ይቀንሳል።

እንደ ቢ.ቢ.ሲ ዘገባ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት ከተዘሩ ሰብሎች መካከል የተለያዩ የአረም አይነቶችን በትክክል ለይተው የሚያውቁ የኤ.አይ ፕሮግራሞችን እያሰለጠኑ ነው።