March 7, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ህንድ ከሩሲያ ነዳጅ እንዳትገዛ የተጣለው ማዕቀብ ለ1 ወር ተነሳላት

ማሻ፤ የካቲት 27/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የአሜሪካ ግምጃ ቤት ህንድ ነዳጅ ከሩሲያ እንዳትገዛ ጥሎት የነበረውን እገዳ ለ1 ወር ማንሳቱን አስታውቋል።

እገዳው ህንድ ገዝታው በባህር ላይ በእግድ ምክንያት ሳይንቀሳቀስ የቆየውን የሩሲያን ነዳጅ እንድታስገባ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የግምጃ ቤቱ ሃላፊ ስኮት ቤሴንት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ እርምጃው ነዳጅ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገባ ያደርጋል ብለዋል።

እገዳው ቀድሞ መንገድ ላይ ለነበረ ነዳጅ የተነሳ በመሆኑ ለሩሲያ እምብዛም ጥቅም እንደማያስገኝም ገልጸዋል።

ለአጭር ጊዜ እንዲቆይ የተደረገው ሆን ተብሎ መሆኑን በመጥቀስም፥ ወደፊት ህንድ ከአሜሪካ የምትገዛውን ድፍድፍ ነዳጅ መጠን ታሳድጋለች ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

አሜሪካ ህንድ የሞስኮን ነዳጅ እንዳትገዛ ጫና በመፍጠር የሩሲያን የገንዘብ ምንጭ ለመቀነስ እየሞከረች ትገኛለች።

በመካከለኛው ምስራቅ አሜሪካ እና እስራዔል በኢራን ላይ የጀመሩትን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ የዓለማችን ዋነኛ የነዳጅ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ በመዘጋቱ ሳቢያ በዓለም አቀፉ የነዳጅና ጋዝ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።