March 5, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የዓለም የቡና ዋጋ በመቀነሱ አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ

የዓለም የቡና ዋጋ በመቀነሱ አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ ዓለም አቀፉን የቡና ገበያ ሁኔታና የኢትዮጵያን ቡና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ይህንን የዋጋ መዋዠቅ ተከትሎ፣ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለቡና አቅራቢዎች፣ ላኪዎችና አርሶ አደሮች ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ሀገሪቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ቡና ያመረተች መሆኑን ያነሱት ዶክተር አዱኛ፤ ከዚህ ውስጥ 600 ሽህ ቶን የሚሆነውን ወደ ውጭ በመላክ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

እንደ ዶክተር አዱኛ ገለፃ ፤ ባለፉት ሁለት ወራት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ከነበረበት 4 ዶላር ወደ 2 ነጥብ 8 ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡

በቀጣይም እስከ 2 ነጥብ 5 ዶላር ሊወርድ እንደሚችል መተንበዩ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፏል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት አቅራቢዎች ቡና ገዝተው ያከማቹ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የዓለም የቡና ገበያ እየቀነሰ በመምጣቱ ምርቱን በእጃቸው ያቆዩ አካላት ለከፍተኛ ኪሳራ እንዳይደረጉ ያላቸውን ቡና አሁን ባለው የገበያ ዋጋ በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡና ወደ ውጭ እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቡናን ከአንድ ዓመት በላይ አሳድሮ ማቆየት፣ በኮንትሮባንድ ወይም በህገ-ወጥ መንገድ ለመሸጥ መሞከር በህግ የሚያስቀጣ መሆኑን አንስተው፤ ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ የሚያሳጣ ተግባር መሆኑንም አመልክቷል።

አቅራቢዎች የዘመኑን መረጃና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዓለም ገበያውን በንቃት እንዲከታተሉና ከኮሜርሻል ቡና ይልቅ የተሻለ ዋጋ በሚያስገኘው የስፔሻሊቲ ቡና ጥራት ላይ እንዲያተኩሩም አሳስበዋል።

ኢፕድ – ጋዜጣ ፕላስ