March 1, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት ኢራን ውስጥ በትንሹ 27 ሰዎች ተገደሉ።

ኢራን በበኩሏ በአካባቢው ሃገራት ውስጥ በሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ በፈጸመችው የአጸፋ ጥቃት ሶስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል። ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በኢራን ላይ የጀመሩት ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በደቡባዊ ኢራን በሚናብ ከተማ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት የ 24 ተማሪዎች ህይወት ማለፉን የኢራን መንግስታዊ የዜና ወኪል አይ.አር.ኤን.ኤ (IRNA) ዘግቧል። ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር እና የሚሳኤል አቅም ለማዳከም ያለመ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸው ነበር።

በአንጻሩ የኢራን አብዮታዊ ዘብ “እውነተኛ ቃል ኪዳን 4” በሚል በሰየመው ዘመቻ በባህሬን በሚገኘው የአሜሪካ 5ኛ የባህር ኃይል ክፍለ ጦር፣ እንዲሁም በቃጣር እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በደረሰ የሚሳኤል ስብርባሪ ጉዳት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ በኢራቅ አንድ ወታደራዊ የጦር ሰፈር በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ዘገባዎች አመልተዋል።

በኢራን መዲና ቴህራን የተፈጸመው የመጀመሪያው የአየር ጥቃት በመንፈሳዊ መሪው አያቶላ አሊ ኻሜኒ ቢሮ አቅራቢያ መፈጸሙ ታውቋል። ነገር ግን ስለደረሰ ጉዳት የተባለ ነገር የለም። የኢራን መንግታዊ የመገናኛ ብዙኃን ከጥቃቱ በኋላ የኢራኑ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜክሽያን በህይወት መኖራቸውን ዘግበዋል። ስለመንፈሳዊ መሪው ግን የተባለ ነገር የለም።

ውጥረቱን ተከትሎ የመካከለኛው ምስራቅ የአየር ክልል በመዘጋቱ ዓለም አቀፍ በረራዎች ተቋርጠዋል።

በቀጠናው እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ሳውዲ አረቢያ፣ ቃጣር እና ባህሬን በግዛታቸው ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶቹን አውግዘዋል። የኤምሬትስ እና የቃጣር አየር መንገዶችን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን ሰርዘዋል። የዓለም የደህንነት ተንታኞች ግጭቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋን ሊያንረው እንደሚችል ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።