March 1, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ከዓድዋ ድል በኋላ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ምን አለች

1888 ዓ.ም በተካሄደው የዓድዋ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያውያን በጋራ ዘምተው ማሸነፍ እና ድል ማድረግ እንደሚችሉ ምስክር ሆነ፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በተጋድሎዋ ያገኘችው የኅብረት ድል ነው፡፡ ድልነቱም የዓለምን ታሪክም የቀየረ ነው፡፡

የቅኝ ገዢዎችን ጭቆና ሲዋጉ ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ኩራት እና የነጻነት ተምሳሌት፡፡

ከዓድዋ ድል በፊት አንድም ሌላ የአፍሪካ ሀገር የአውሮፓ ጦርን አሸንፎ አያውቅም። ኢትዮጵያውያን ግን አደረጉት፡፡

በሌሎች ሀገራት የተቃውሞ ውጊያዎች ቢደረጉም ውጤት ግን አላስገኙም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የዓድዋን ድል ስትቀዳጅ ዜናው በመላው ዓለም ናኘ። ድሉ የዓለምን የተዛባ ዕይታ የቀየረ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።

ዜናውም መላውን የአውሮፓ ምድር ያስደነገጠ እና ያስገረመም ነበር።

የታሪክ ምሁራን፣ መፅሔቶችና ጋዜጦች ስለ ዓድዋ ብዙ ብለዋል፡፡

ለአብነትም ዘ ዋሺንግተን ኢንፎርመር (The Washington Informer) የኢትዮጵያውያን ድል በዓለም ዙሪያ ፍርሃትን መፍጠሩን አትቷል።

የእነማርከስ ጋርቬይ እና የኔልሰን ማንዴላን የነጻነት ትግል ማበረታታቱንም ይጠቁማል።

ዋሺንግተን ፖስት በበኩሉ ከላይቤሪያ በስተቀር የአፍሪካ ሀገሮች በአውሮፓዊያን ቅኝ ግዛት ሥር ሲገቡ፣ ኢትዮጵያ ግን የጣሊያንን ወራሪ ጦር አሸንፋ ብቸኛ ነፃ የአፍሪካ ሀገር ሆና መቆየቷን ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ስኬት የተገኘው በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው አንድነት፣ አስተዋይ አመራር፣ አስፈሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ሀገሪቱ ረዥምና ዘላቂ ታሪክ ያላት ስለመሆኑ እና የሕዝቡ የአልደፈር ባይነት መንፈስ መሆኑንም ያትታል፡፡

ከድሉ በኋላ የጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያን እንደ የነጻነትና የክብር አርማ አድርገው ማየት ጀመሩ። የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ጽንሰትም ይኸው ነው፡፡

ሬይሞንድ እንደጻፈው ምንም እንኳን የዘረኝነት አመለካከቶች ባይወገዱም ድሉ የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ሥርዓት ፈታኝነትን ቀንሷል ይላል።

ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ሕዝቦችን አስከብሯል።

በፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሀሳብ ላይ አወንታዊ ሚና አሳርፏል፡፡

እንዲሁም የአፍሪካዊያንን የነጻነት እንቅስቃሴዎችን አነሳስቷል።

ጣሊያንን ጨምሮ ዋና ዋና ቅኝ ገዢዎች ለኢትዮጵያ ነፃነት ዕውቅና ሰጥተዋል።

በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ የአውሮፓ ሀገራት ቆንስላዎች ተከፍተዋል።

የንጉሡ ምኒሊክ ባለቤት የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጠንካራ ድጋፍም ድሉን ለውጤታማነት እንዳበቃው ሬይሞንድ ጆናስ መስክሯል።

እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት የዓድዋ ድል ከትግል ባሻገር በደቡብ አፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚል የሃይማኖት አስተምሮ እንቅስቃሴን ያስጀመረ ታሪካዊ ከስተት ነው።

የዓድዋ ድል የጣሊያን መንግሥት እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል።

ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ተገደዋል።

ጃማይካዊው ፖለቲከኛ ማርከስ ጋርቬይ፣ አሜሪካዊው የጥቁር ሕዝቦች ተቃውሞ መሪ የነበሩት ዊሊያም ድ ቦይስ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ጆርጅ ፓድሞር እና ለሌሎችም የዓድዋ ድል ለትግላቸው መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል፡፡

ማርከስ ጋርቬይ እንደጻፈው ዓድዋ ጥቁሮችን ከአፍሪካ ጥንታዊ ክብር እና የወደፊት ተስፋ ጋር አገናኝቷል፡፡

ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገባው “ኢትዮጵያዊያን የወረራቸውን ሰራዊት በዓድዋ ተራሮች ድል አደረጉት፤ ሁለቱም የባራቶሪ ሠራዊት ክንፎች በኃይል ጥቃት ተሸንፍው ነበር” በማለት አስነብቧል፡፡

መልካም 130ኛ የዓድዋ የድል በዓል!

እኛም የዓድዋ ጀግኖች እናቶችና አባቶች ልጆች ነን!