February 25, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሸካ ዞን ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በየኪ ወረዳ ተገኝተው የመስክ ምልከታ አካሄዱ

ማሻ፤ የካቲት 17/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የዞኑ ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በየኪ ወረዳ ሚቺና በጪ ቀበሌዎች ተገኝተው የትምህርት ስራንና የጤና ጣቢያ አገልግሎት አስጣጥ ያለበትን ደረጃ የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።

የምክር ቤቱ ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በየኪ ወረዳ ሚቺ ቀበሌ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የ2018 ዓ.ም መደበኛ እና ቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የመማርና ማስተማር ስራ ያለበትን ደረጃ ምልከታ አድርገዋል።

ትምህርት ቤቱ በህብረተሰብ ተሳትፎና በወረዳ አስተዳደር ድጋፍ በ2.6 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መማሪያና መመገቢያ ክፍል ግንባታ 75% ላይ እንደሚገኝ በድጋፋዊ ክትትል ወቅት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መምህር መሀመድ ጌታ መሀመድ ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ መድህኃኒት ማሞ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ በትምህርት ስራው ላይ እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው ያለውን የውስጥ ሀብት በአግባቡ ሰብስቦ ለትምህርት ስራው መጠቀም እንዳለበት ገልፀዋል።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ በመስክ ምልከታቸው የበጪ ጤና ጣቢያ አገልግሎት አሰጣጥ ያለበትን ደረጃ በጤና ጣቢያው ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።በጤና ጣቢያው የነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል፣የእናቶች ማቆያ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመድኃኒት ግዢ፣የወባ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራ፣ የአንቡላንስ አገልግሎት፣ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተመልክተዋል።

የበጪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2018 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራ ያለበትን ደረጃ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት የ9ኛና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ሂሳብ የትምህርት ዓይነት እየተማሩ እንዳልሆነ እንዲሁም የእንግሊዝኛና የኢኮኖሚክስ የትምህርት ዓይነቶች ላይ የመምህራን እጥረት መኖሩ በመማር ማስተማር ስራው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር  አሸናፊ ንጉሴ የገለፁ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴዎችም ችግሩ መኖሩን በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ ችለዋል።

ትምህርት ቤቱ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ተማሪዎች የአይ ሲቲ የትምህርት አይነት ከቲዮሪ ባለፈ የተግባር ትምህርት እየወሰዱ እንዳልሆነ፣የመምህራን በስራ ገበታ ላይ ተረጋግቶ ተቀምጦ የማስተማር ስራውን እየሰሩ እንዳልሆነ በመስክ ምልከታው ለማረጋገጥ ተችሏል።

የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በግብረ መልሳቸው በመስክ ምልከታው ላዩዋቸው ክፍተቶች ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የበጪ ጤና ጣቢያን የመጠገን ስራ ለመስራት እቅድ መያዙንና የጤና ጣቢያውን የውስጥ ችግር ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተደረገ በመሆኑ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።

የበጪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን አምነው ከትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ጋር በመነጋገር የሚፈታ መሆኑን ገልፀው የሂሳብ መምህራንን ቅጥር ለመፈፀም ገበያ ላይ መምህራንን ማግኘት አለመቻሉ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረው የቋንቋ መምህር እጥረትን ለመፍታት ትርፍ ካለበት ትምህርት ቤቶች በዝውውር ክፍተት ወደታየበት ትምህርት ቤቶች የመመደብ ስራ ይሰራል ብለዋል ሲል የዘገበው የኪ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።