ማሻ፤ ጥር 12/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በግልና በቡድን ለተደራጁ አነስተኛ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ለመስጠት የውል ስምምነት ተፈራረመ።
የውል ስምምነቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሪጂን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መልካሙ ደሲሳ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በጋራ ተፈራርመዋል።
ባንኩ የሰብል ምርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ እንስሳት እርባታ፣ ምርት ማከማቻ መጋዘን እና የግብርና ማሽነሪዎች የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ያደረገ ነዉ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት ጊዜያት መንግሥት ለግብርና ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ዘርፉ እየተነቃቃ ቢሆንም ለግብርና ዘርፍ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ባለመቻቸቱ በሚፈለገው ልክ ውጤት ሳይመዘገዘብ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገሪቱ ጀርባ እጥንት የሆነው ግብርና ዘርፍ በመደገፍ ለአርሶ አደሮችና እና አርብቶ አደሮች የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ለመስጠት የውል ስምምነት በመፈጸሙ አመስግነዋል።
ይህም በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋለው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረትን በመቅረፍ የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ፣ ዘርፉን የሚያዘምን እንዲሁም ለአርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ሚናዉ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገለጹት።
ባንኩ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮችና እና አርብቶ አደሮች የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ለመስጠት ከገባው ውል በተጨማሪም ለክልሉ መንግስት እና በክልሉ በተለያዩ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የፋይናንስ ብድር አገልግሎት እንዲያመቻች አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደቡብ ሪጂን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መልካሙ ደሲሳ በውል ስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ባንኩ ባለፉት ጊዜያት በንግድ ዘርፍ የሚሰማሩ ነጋዴዎችና ለሌሎች ተቋማት የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ባንኩ በክልሉ በግልና በቡድን ለተደራጁ አነስተኛ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ለመስጠት ውል ፈጽሟል ያሉት ምክትል ፕረዚዳንቱ ለተፈጻሚነቱ የጋራ ትብብር እንዲጠናከርም ገልጸዋል።
የፋይናንስ ብድር አገልግሎቱ የግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን እውን የሚያደርግ፣ ግብርና ዘርፉን የሚያዘምን፣ ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ሁሉ ማግኘት እንዲችል የሚያግዝ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ዕድል መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።
More Stories
ዜጎች በመልዕክት መላላኪያ አማራጮች በሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር
በሸካ ዞን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያለመ ዞናዊ የፀጥታ ግብረ ኃይል የምክክር መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሄደ
ክልላዊ የተቀናጀ የማኅበረሰብ አቀፍ ተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ ፕሮግራም በመካሄድ ላይ ይገኛል።