ማሻ፣ ጥር 06/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቱሪዝምና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግሥት የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው በጉባ በተካሄደው “ስለ ኢትዮጵያ” የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ መንግሥት በሕዳሴ ግድቡ፣ በደሴቶችና በንጋት ሐይቅ አካባቢ ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የመሬት አቅርቦትን በሊዝ እና በተለያዩ አማራጮች ያመቻቻል።
በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት ሥራው የሚሆን የፋይናንስ ብድር በባንኮች በኩል እንዲመቻች እንደሚደረግና ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከውጭ ሲገቡ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።
በሪዞርቶች፣ በሎጅዎችና በሌሎች የቢዝነስ አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሠራተኛ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የሰው ኃይል እጥረትን ለመቅረፍ በቁልፍ የአመራር ቦታዎች ላይ የውጭ ባለሙያዎችን ለማምጣት እንደሚፈቀድ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለሀብቶች በሆቴል፣ በሬስቶራንት፣ በውኃ ትራንስፖርትና በኩነት ዝግጅት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ማበረታቻ በግድቡ ዙሪያ የሚገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
More Stories
ዜጎች በመልዕክት መላላኪያ አማራጮች በሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር
በሸካ ዞን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያለመ ዞናዊ የፀጥታ ግብረ ኃይል የምክክር መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሄደ
ክልላዊ የተቀናጀ የማኅበረሰብ አቀፍ ተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ ፕሮግራም በመካሄድ ላይ ይገኛል።