February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ምርጫ ቦርድ ዲጂታል የመራጮችና ዕጩዎች የምዝገባ ሥርዓትን አስጀመረ

ማሻ፣ ታህሳስ 27/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2018 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ የሚያስችሉ ሁለት የሞባይልና የድረ ገጽ መተግበሪያዎችን ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ዲጂታል የመራጮችና የዕጩዎች የምዝገባ ሥርዓት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብርን እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ የምርጫ ሂደትን ግልጽ በማድረግ ታማኝነትን ለመገንባት በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሠራር ሥርዓት ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምርጫን በቴክኖሎጂ መደገፍ በርካታ ሀገራት ውጤታማ የሆኑበት አሠራር መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ቦርዱ ያበለጸጋቸው መተግበሪያዎች ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን ከመቆጠብና እንግልትን ከመቀነስ ባለፈ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያ የምታካሂደው አጠቃላይ ምርጫ ነጻና ገለልተኛ ለማድረግ ያግዛሉ ብለዋል።

ቴክኖሎጂን ከማልማትና ከመጠቀም ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቶ ቴድሮስ ምህረት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ሥርዓቱን ለሥራ ቅልጥፍና፣ ለመረጃ ትክክለኛነት፣ ለአካታችነት እና ወጪን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።

ቦርዱ የዕጩዎችን ምዝገባ ሙሉ በሙሉ፣ የመራጮችን ምዝገባ ደግሞ በከፊል በቴክኖሎጂ ታግዞ ለማከናወን መዘጋጀቱን አስታውቋል።

መተግበሪያዎቹ መራጮችና ተመራጮች ባሉበት ሆነው እንዲመዘገቡ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል