December 17, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በጋራ ስንቆም ከተራራ የገዘፍን ከብረት የጠነከርን ስለመሆናችን ህያው ምስክር ነዉ :-ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋገሾ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅን አስመልክቶ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በተለያዩ ትዕይንቶች ታጅቦ በስኬት ተጠናቋል ።

በኅብረት ችለናል በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደዉ የድጋፍ ሰልፍ መርሃ -ግብር ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋገሾ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በጋራ ስንቆም ከተራራ የገዘፍን ከብረት የጠነከርን ስለመሆናችን ህያው ምስክር ያሉ ሲሆን ግድቡ በላባችን በደማችንና በሀብታችን ያፀናነዉ ህያዉ የምህንድስና ጥበብና የማህበረተሰብ የወል ቅርሳችን ነዉም ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ የማንሰራራታችን ብስራት እንዲሁም ጥልቅ የሀገር ስሜት ማሳያ የሆነ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል ።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የነበሩትን የዉስጥና የዉጪ ጫናዎች ሳንበገር ኢትዮጵያዊያን በህብረት በመቆም በስኬት አጠናቀን ለምረቃ አብቅተናል እናም በህብረት ችለናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ለሀገራችንና ለህዝባችን ጥቅም ከቆምን ከከፍታ ጉዛችን የሚያስቆመን ምድራዊ ሀይል የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የህዳሴ ግድብ ዉስብስብ ችግሮችን ተሻግረን እንዳጠናቀቅነዉ ሁሉ ወደ ላቀ ከፍታ ጉዞ በአንድነት መነሳት ይኖርብናል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ።

በመረሃ- ግብሩ የተገኙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ደም የከበረ በላባቸዉ የታሰረ የታሪካችን ማህተም የህልዉናችን አሻራ በመሆኑ የዚህ ትዉልድ አካል በመሆናችን ልንደሰት ይገባል ብለዋል።

የካፋ ዞን ህዝብ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 143 ሚልዮን ብር በላይ ቦንድ ጊዥ በማካሄድ የአጋርነት ሚና ሲወጣ መቆየቱን ገልፀዋል።

ይህ የዞኑ ህዝብ ድጋፍም በለሎች ሀገራዊ የስራ መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኅብረት ችለናል በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ መረሃ-ግብር ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋገሾ፣የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሁሉም ዞኖች ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ – ቸርነት አባተ