July 10, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ቼልሲን ለፍጻሜ ያበቁ ግቦችን ያስቆጠረው ጆአዎ ፔድ…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ቼልሲን የተቀላቀለው ጆአዎ ፔድሮ በልጅነት ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን የፍጻሜ ተፋላሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ብራዚላዊው የፊት መስመር ተጫዋች ፔድሮ ከብራይተን ቼልሲ ከተቀላቀለ በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረግም በላይ ቼልሲን ለፍጻሜ ያበቁ ሁለት የአሸናፊነት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

የልጅነት ክለቡ ፍሉሚኔንሴ ላይ ሁለት ድንቅ ግቦችን በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ ያስቆጠረው ፔድሮ የጨዋታው ኮከብ መባሉ አይዘነጋም፡፡

ከሳምንት በፊት በ55 ሚሊየን ፓውንድ ቼልሲን የተቀላቀለው ፔድሮ በፍሉሚኔንሴ ጨዋታ ሶስት ሙከራዎችን አድርጎ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

አዲሱ ፈራሚ ፔድሮ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ”በአጀማመሬ ደስተኛ ነኝ፤ አሁን የፍፃሜው ጨዋታ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን” ሲል ተናግሯል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ አሰልጣኝ ማሬስካ ብራዚላዊውን የፊት መስመር ተጫዋች ፔድሮን ከማስፈረማቸው በፊት ከቀድሞ የተጫዋቹ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲዘርቢ ስለ ተጫዋቹ ጠይቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የ23 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ፔድሮ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለብራይተን በሊጉ ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስቆጥሮ 6 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ከሳምንት በፊት ቼልሲን ከብራይተን የተቀላቀለው ተጫዋቹ ቼልሲ በክለቦች ዓለም ዋንጫ ከፓልሜራስ ጋር ባደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን ለአዲሱ ክለቡ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በክለቦች ዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ ጨዋታውን የጀመረው ተጫዋቹ ሁለት ድንቅ ግቦችን የልጅነት ክለቡ ፍሉሚኔንሴ ላይ በማስቆጠር አዲሱ ክለቡ ቼልሲን የፍጻሜ ተፋላሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ፔድሮ ከሀገሩ እና ከልጅነት ክለቡ ፍሉሚኔንሴ በመቀጠል በሻምፒዮን ሺፕ ለዋትፎርድ ከተጫወተ በኋላ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለብራይተን መጫወቱ ይታወሳል፡፡

ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በብራይተን ቤት ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ፔድሮ ለሀገሩ ብራዚል በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ግልጋሎት መስጠት ችሏል፡፡

ባለፉት ዓመታት ቼልሲ የፊት መስመሩን ለማጠናከር በርካታ ሚሊየን ፓወንድ ወጪ አድርጎ ወደ ስብስቡ የቀላቀላቸው ተጫዋቾች ሁሉም ባይባሉም በሚፈለገው ልክ ክለቡን እያገለገሉ አይገኙም፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ምዕራብ ለንደን የደረሰው ፔድሮ የቼልሲን የፊት መስመር ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኤፍ ኤም ሲ