July 4, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት የሚል ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማሻ ፣ የሰኔ 26፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ለግብርናው ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት የሚል ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ አርሶ፣ ኮትኩቶ መዝራት ብቻም ሳይሆን ብዙ ግብዓቶች በመጠቀም፣ ጠቅላላ ሰንሰለቱን በመለየትና በማወቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት መልኩ ፅኑ እምነት ተይዞ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገቱ ግብርና ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉትጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ዘርፉን ለማዘመን ባከናወናቸው ተግባራትም ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት 31.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ መቻሉን ገልጸው፣ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ዘንድሮ ከዓምናው የ300 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመጨመር 1.5 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታት ከ220 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚችል 20 የሚጠጉ የመስኖ ግድቦች በመንግስት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም በዚህ ዓመት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ 84 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ 6 ከፍተኛ የመስኖ ግድቦች እንደሚመረቁም አመላክተዋል፡፡

በክልሎች ለምርት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት የሚፈስባቸው የበጋ መስኖ ልማትን የሚያግዙ ከ100 በላይ አነስተኛና መካከለኛ ግድቦች ይሰራሉም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 27 ሚሊዮን በሴፍቲኔት የተያዙ ዜጎች እንደነበሩ በማንሳት፣ እነዚህን ዜጎች ከሴፍቲኔት ለማሸጋገር ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በዚህም በራሳቸው ወደ መተዳደር በማሸጋገር 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነጻ ወጥተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ቀሪውን ከ4 ሚሊዮን ያላነሰ ተረጂም ነጻ በማውጣት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ማድረግ አለብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡

ግብርና ቢዚህ ዓመት 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንዲያመጣ መታቀዱንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢቢሲ