ማሻ ፣ የሰኔ 02፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለክልሎች የሚከፋፈለው የጋራ ገቢ የድጎማ በጀት እያደገ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
በውስን ዓላማ የድጎማ በጀቶች ትልልፍ እና በጋራ ገቢዎች ክፍፍል በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ላይ የዳሰሳ ጥናት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉብኤ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር አንዱ ሲሆን በክልሎች የድርሻ ክፍፍል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱንም ጠቁመዋል።
የክልሎች የጋራ ገቢ የድጎማ በጀት ክፍፍል ከለውጡ በፊት ከነበረበት 4 ቢሊዮን ብር ወደ 70 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማደጉን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
ውስን ዓላማ የድጎማ በጀቶች ላይ የግልጸኝነት እና የተጠያቂነት ችግሮች ሲነሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ገቢ በሕግ አግባብ ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች መተላለፉን እንዲሁም ፍትሐዊነት፣ ግልጽነት፣ አሳታፊነት እና ተጠያቂነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል።
በተጨማሪም ክፍተት ያሉባቸው ጉዳዮችን በመለየት ለሚመለከታቸው አካላት ግብረመልስ በመስጠት እንዲታረሙ ለማድረግ እንደሚያስችል አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው በውስን ዓላማ የድጎማ በጀቶች ትልልፍ ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱ የግልጽነት፣ የአሳታፊነት፣ የግንዛቤ እና የተጠያቂነት ችግሮች መኖራቸውን አመልክቷል።
የምክር ቤቱን የአሠራር ሥርዓት ተከትሎ ከመሥራት አንፃር ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውም ነው የተገለጸው።
በ2017 በጀት ዓመት ከ215 ቢሊዮን ብር በላይ ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች ለክልሎች መተላለፋቸው ተመላክቷል።
ኢቢሲ
More Stories
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ጀመረ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት አመት የአስፈፃሚ አካላት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።