June 4, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ሀገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው-የፌደራል ተቋማትና ማህበራት ተሳታፊዎች

ማሻ ፣ የግንቦት 24፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ‎ የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግና ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህልን ለማዳበር ሀገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና እንዳለው የፌደራል ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

በእስካሁኑ ሂደትም 38 የፌዴራል ተቋማትና ማህበራትን የወከሉ አጀንዳዎችን ለዋናው መድረክ አቅርበዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ በየጊዜው ለሚከሰቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የምክክር ባህልን ማዳበር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ለትውልዱ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ከገንዘብ ሚኒስቴር በውይይቱ የተሳተፉት ሃይሉ በጆ፣ የማያግባቡ ሀሳቦችን በምክክር መፍታት የስልጣኔ ምልክት ነው።

ከዚህ አኳያ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው ሁሉ በሀገር ጉዳይ በጋራ ለመምከርና የተሻለ ሀገር ለመገንባት የጀመሩት ምክክር ለሀገር ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ይፍቱ አባስ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የምክክር ባህልን ለማዳበርና ዜጎች ጥያቄ ሲኖራቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ እንዲችሉ መሰረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዮሴፍ አበራ ወጣቱ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ገልጿል።

ከዚህ አኳያ ለሀገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ አጀንዳዎችን በማቅረብ የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚገባም ጠቁሟል።

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ወጣቱ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነትና በዓለም ስላላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት በቂ ዕውቀት እንዲኖረው ማድረግ አለብን ይላሉ።

ዓለም ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ ግምት እንዳለውና አዲስ አበባም የተለያዩ የዓለምአቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች መቀመጫ ከመሆኗ ባለፈ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ከተማ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

ወጣቱ አባቶቹ ያስረከቡትን ገናና ሀገር ጠብቆና አበልጽጎ ለማቆየት ችግሮችን በሰከነ መንገድ የመፍታት ባህልን ሊያዳብር ይገባል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የተወከለችው አሜን ግርማ በበኩሏ፥ ምንም እንኳን የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያ የሁሉም ሀገር በመሆኗ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብላለች።

ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተወከለችው እስከዳር ግርማ በበኩሏ፣ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማሳተፉ አካታችነቱን እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት ህትመት አሰፋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አለኝ የሚላቸውን አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ማቅረቡ የዴሞክራሲ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግና ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህልን ለማዳበር ሀገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የቀድሞው መከላከያ ሰራዊት አባል ሻለቃ ጀምበሬ ተሰማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ በጋራ ጉዳይ ላይ ለመመካከር ያለው ፍላጎት ሀገር ለማሻገር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ገነት ማርቆስ፥ ኢትዮጵያ ትልቅ የልማትና ዕድገት ተስፋ ያላት ሀገር በመሆኗ ለትውልዱ የተሻለ ሀገር ለማስረከብ ምክክሩ ትልቅ መሰረት የሚጣልበት መሆኑን አንስተዋል።

ከትናንት በስትያ የተጀመረው የፌደራል የተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢዜአ