May 21, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ያለማቋረጥ በመተግበር ምሳሌ ሆናለች – ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር)

ማሻ ፣ የግንቦት 12፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ያለማቋረጥ ለተከታታይ ዓመታት በመተግበር ምሳሌ መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ኢኮሎጂ እና ብዘኃ ህይወት ተባባሪ ፕሮፌሰር ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች የብዘኃ ህይወት ሃብት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማስቻሉን ገመዶ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

የመሬት ውሃ የመያዝ አቅም እንዲጨምር ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጎርፍ፣ ድርቅና መሰል አደጋዎችን መቋቋም ማስቻሉን አመላክተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ መርሐ ግብሮች እና ፕሮጀክቶች ለማህበረሰቡ ከፍተኛ የሆነ የጤና ጠቀሜታ ማሰገኘታቸውን ጠቅሰው÷ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ጭምር ያነሱት ገመዶ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ያለችውን መፈጸም የምትችል ሀገር መሆኗን ለተቀረው ዓለም በማሳየት ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትን አትርፋበታለች ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ እየደገፉ መሆናቸውን አንስተው÷ የተጀመረው እና በውጤታማነቱ የቀጠለው መርሐ ግብሩ ከዘመቻ ባለፈ በተቋም ደረጃ መመራትና መደገፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አጽዋት ለህጻናት የአዕምሮ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ገመዶ (ዶ/ር)÷ ትውልዱ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ኅብረተሰቡ መኖሪያ አካባቢውን በእጽዋት በመሸፍን ነፋሻማ እና አረንጓዴ ስፍራን መፍጠር ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።

ፋና