May 21, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ ነው – ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ

ማሻ ፣ የግንቦት 13፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ገለፁ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ከኢቲቪ በነበራቸው ቆይታ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በጤና ባለሙያዎች ዘንድ የታየው እንቅስቃሴ የሙያ ቃል ኪዳንን የላከበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሙያዎች ሊመለሱ ይገባል የሚሏቸውን ጥያቄዎች ስራ በማቆም ሳይሆን የተሰጣቸውን ሃገራዊ ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ክስተት በተወሰነ መልኩ የአገልግሎት መስተጓጎል ቢኖርም በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም የጤና ተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አሁን የመጣ ሳይሆን ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግስት በእነዚህ ዓመታት ጥያቄዎቹን ለመመለስ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ የገባው የጤና አስተዳደር አዋጅ የጤና ባለሙያዎችን የዓመታት ጥያቄ በሂደት ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በአዋጁ መሰረት የጤና ባለሙያዎች ነፃ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራርን እና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የጤና ሙያተኛውን በጥቅማ ጥቅምና በሌሎች ሁኔታዎች ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት፡፡