May 20, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት መጀመር በአቅራቢያችን ህክምና እንድናገኝ አስችሎናል-ነዋሪዎች

ማሻ ፣ የግንቦት 12፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በሸካ ዞን የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት መጀመር ህክምና በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

በሆስፒታሉ ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎች ቀደም ሲል በአካባቢያቸው በሆስፒታል ደረጃ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ተቋም ባለመኖሩ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከተገልጋዮቹ መካከል በቀዶ ሕክምና ወንድ ልጅ የተገላገሉት የማሻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ አምበሎ ጤና ተቋሙ እንደደረሱ ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

“ሀኪሞች ተረባርበው ነፍሴን ታድገውኛል፤ ከፈጣሪ በታች በሙያቸው ረድተው ልጅ ስላስታቀፉኝ ደስ ብሎኛል” ሲሉም ገልጸዋል።

ከጤና ጣቢያ ምጥና ሕመማቸው ሲበረታ ወደ ሆስፒታሉ መላካቸውን የገለጹት ወይዘሮ በላይነሽ፣ በአቅራቢያቸው የተገነባው ሆስፒታል በጤና ባለሙያዎች የተሻለ አገልግሎት በማግኘታቸው ልጃቸውን በሰላም መውለዳቸውን ተናግረዋል።

ከማሻ ወረዳ ልጃቸውን ለማሳከም የመጡት አቶ አበበ ገንጃ በበኩላቸው ከዘጠኝ ወራት በፊት ከፍተኛ ህክምና ለማግኘት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ በአስቸጋሪ መንገድ ይጓዙ እንደነበር አስታውሰዋል።

የማሻ ሆስፒታል በአቅራቢያቸው መገንባቱ ከብዙ እንግልት እንደታደጋቸው ገልጸው፣ ምሽት ላይ በሆስፒታሉ ቢደርሱም ባገኙት አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ የወላድ እናቶችን መከራ ያስታገሰና የድሃን እንባ ያበሰ ከመሆኑም በላይ ያመመንን በቋንቋችን ተናግረን ለማስረዳት ዕድል ፈጥሮልናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዝናዬ አስፋው ናቸው።

በሆስፒታሉ የተሟላ የጤና አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ነርስ ታምራት ተፈሪ ባለው አቅምና ሙያ ለህብረተሰቡ ተገቢ ግልጋሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

“በተለይ ወላድ እናቶችንና ሕጻናትን የመንከባከብ ሙያዊ ግዴታችንን እየተወጣን ነው” ያለው ነርስ ታምራት፣ ሆስፒታሉ አዲስ በመሆኑ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማጠናከር ግብአት የማሟላት ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ኅብረተሰቡን የማገልግል ሃላፊነት ቀንና ማታ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሆስፒታሉ የላቦራቶሪ ክፍል ባለሙያ አስናቁ ዋና ናቸው።

“ሆስፒታሉ አዲስ በመሆኑ የባለሙያ እጥረት ቢኖርም ክፍተቱን በመሙላት ለታካሚ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የማሻ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክቡርሰው ዓለሙ እንደገለጹት የሆስፒታሉ አገልግሎት መጀመር ለአካባቢው ማኅበረሰብ በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል።

ከማሻ ከተማ ባሻገር በሸካ ዞን ላሉ ወረዳዎች እና አጎራባች ዞኖች ጭምር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም አገልግሎቱን ለማጠናከር ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ ተመርቆ ወደ አገልግሎት መግባቱ የሚታወስ ነው።

ኢዜአ