May 17, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በ2017 ዓ/ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ከ399 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ ይካሄዳል፦ አቶ ማስረሻ በላቸው

ማሻ ፣ የግንቦት 08፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2017 ዓ/ም የበልግ ወቅት ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ተከላ መርሃ ግብር ማብሰሪያ ፕሮግራም በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ በጠመንጃ ያዥ ቀበሌ ተካሂዷል ።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ያስጀመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በእስካሁኑ በክልሉ 1.3 ቢሊዮን የደን፣ ጥምር ደን፣ ፍራፍሬ፣ ቡና እና ሌሎችን በመትከል የክልሉን ስነምህዳር መቀየር መቻሉን የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ካለው ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት የተነሳ በበልግ ወቅትና በመደበኛው ክረምት መርሃ ግብር ተከላ እንደሚካሄድ ገልጸዋል ።

በአምናው ተከላ በ8ሺ ሄክታር መሬት ላይ ከ48 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት አቶ ማስረሻ በ2017 ዓ/ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ 399 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች ተከላ እንደሚካሄድ አስረድተው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የነገ ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስንና ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍቸኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

አክለውም በርካታ ህዝብ በመሣተፍ እየተከሉ መሆኑንና በርካታ ውጤት የተመዘገበበት ዘርፍ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ጨምረው ገልጸዋል ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትን በማስተላለፍ በወረዳው በሰፊ ማሳ የሚገኘውን የባህር ዛፍን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባላቸው ተክሎች ለመተካት እየተሰራ መሆኑ የገለጹት የሰሜን ቤንች ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ስንታዬሁ በፍቃዱ ናቸው።

በመጨረሻ በወረዳው የባህር ዛፍ ተክልን በመቁረጥ በ4 ቀበሌዎች በተለያዩ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባላቸው እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አጋዥ የሆኑ እንደ ሙዝ ያሉ የፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም በበቆሎ በትኩረት እየለማ ያለውን ማሳ እና ግንባታው የተጠናቀቀው የፍራፍሬ ግብይት ማዕከል ጉብኝት ተደርጓል።

ክልል ኮሚኒኬሽን