ማሻ ፣ የግንቦት 07፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ66 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷ በግብርናው ዘርፍ በበጋና በልግ ወቅት የግብርና ስራዎች የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የግብዓት አቅርቦትና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችና ሌሎችም በርካታ መርሐግብሮች በትግበራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በበጋ ስንዴ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መልማቱን አንስተው÷ ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን ከ66 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የበልግ አዝመራ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው፥ ከዚህም ውስጥ 235 ሺህ ሄክታር በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ የተሸፈነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ እስከ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም ድረስ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች በጉልበት የተሳተፉበት 5 ሚሊየን ሄክታር የሚሸፍን የተቀናጀ የተፋሰስ ሥራ መከናወኑንና ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት መሆኑን አንስተዋል።
ዘንድሮ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መመደቡን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚገዛው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ለዘንድሮ የምርት ዘመን በማዳበሪያ ዋጋ ላይ መንግስት የ84 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን አመላክተው÷ ይህም በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከ5 ሺህ ብር በላይ ድጎማ እንደሚደረግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ለቀጣይ ምርት ዘመን እስካሁን 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደብ መድረሱንና ከዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ወደ ክልሎች መሰራጨቱን እንዲሁም ቀሪውን የማጓጓዙ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰብስቦ 400 ሺህ ኩንታል ለእርሶ አደሩ መሰራጨቱን በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል፡፡
ፋና
More Stories
ምርታማነትን በማሳደግ የተሟላ ሃገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ከሁሉም አባላት ይጠበቃል፦አቶ የሺዋስ ዓለሙ
ምክር ቤቱ አራት ስምምነቶችን አጸደቀ
ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎች መከፈት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እያሳደገ ነው