May 15, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሞዴፓ ከሌሎች የሀገሪቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለህዝቡ ተጠቃሚነት ተግቶ እንደሚሰራና በሀገሪቱ ነፃ የምርጫ ምህዳር እንዲጠናከር የበኩሉን እንደሚወጣ ገለፀ ።

ማሻ ፣ የግንቦት 07፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ሞዴፓ/ ትብብርና መቻቻል ለጋራ ሀገረ መንግስት ግንባታ በሚል መሪ ቃል 3ተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሸካ ዞን ማሻ ከተማ አካሂዷል።

በጉባኤው የፓርቲውን የስራ አፈፃፀም ረፓርት ያቀረቡት የቀድሞ የሞዴፓ ፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ዘለቀ ሞዴፓ ሲመሰረት በርካታ ገፊ ምክንያቶች እንደነበሩ ገልፀው አሁንም ለህዝቡ ህገመንግስታዊ መብት መከበር በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት በማጠናከር በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረው ከአቻ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት በመስራት በሀገር ደረጃ ውጤታማ ለውጥ ለማስመዝገብ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል ።

ከሌሎች በሀገሪቱ ከሚገኙ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለህዝቡ ተጠቃሚነት ተግተው እንደሚሰሩ ገልፀው ነፃ የምርጫ ምህዳር መጠናከር እንዳለበት እንዲሁም ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ቀጣይ የሚደረገው ምርጫ ውጤታማ እንዲሆን እንተጋለንም ብለዋል።

አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩትን ደን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሁላችንም በጋራ መስራት አለብን ያሉት አቶ ብርሃኑ ፓርቲው ከተመሰረተ ወዲህ በዚህ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱን ገልፀዋል ።

ለህዝቡ ተጠቃሚነት ፓርቲው የጀመረውን ሰላማዊ ትግል የሚያስቀጥል ቢሆንም ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ባገናዘበ መልክ ለሀገር ሰላምና ለውጥ በጋራ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳዳሪ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴና ቀጣይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል ።

የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በመድረኩ ላይ የተገኙት የፓርቲው አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሀሳብና አስተያየት በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል ።

በጉባኤው የተሻሻለው የፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ ፣ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ያከናወናቸው የስራ ሪፖርት በማድመጥ እንዲሁም የአመራርና ቁጥጥር ኮሚሽን ምርጫ በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል ።

በመጨረሻም ቀጣይ ሶስት አመታት ፓርቲውን የምመሩ አካላት በመምረጥ የስልጣን ርክክብ የተደረገ ሲሆን በዚህም አቶ አለማየሁ ሻረው የሞቻ ዴሞክራሲያዉ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ፣.አቶ ብርሃኑ ዘለቀ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ፣አቶ አድሱ አምበሎ ምክትል ፕሬዚዳንት በማድረግ እንዲሁም ለሎች ስራ አስፈፃሚዎችንም በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል።

ዘጋቢ ወንድማገኝ ገሪቶ