ማሻ ፣ የግንቦት 04፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) 3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ግንቦት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።
ጉባኤው ከጂ20 ኢንተር ፌዝ ፎረም፣ ከአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካ ህብረት ስር ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪዎችና ሌሎችም ይሳተፉበታል።
እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከ80 በላይ የሚሆኑ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የባህል መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ምሁራን በጉባኤው ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።
ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያተኩራል።
እንዲሁም በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በትምህርትና ሌሎች የልማት አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር ለቡድን 20 አባል ሀገራት ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መከባበርና የአብሮነት ልምድ እንደሚቀስሙ እና በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችና ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኙ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ መረጃ ጠቁሟል።
ፋና
More Stories
ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎች መከፈት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እያሳደገ ነው
የእናትነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 39ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ