ማሻ ፣ የግንቦት 04፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መከፈታቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ማስቻሉ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የበርካታ ሀገራት ኢንቨስተሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ የውሃ ሀብት፣ ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል እንዲሁም የተሟላ መሰረተ ልማት ያላት ሀገር መሆኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተገበረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያመጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳሩን የመክፈት እርምጃዎችም ትልቅ ውጤት እያመጡ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸው፤ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት በማረጋገጥ ለኢንቨስተሮች ምቹ አቅም መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ወደ ሥራ መግባቱም ተወዳዳሪ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በለውጡ ዓመታት መንግሥት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት መመዘገቡን አንስተዋል፡፡
ፎረሙ ትብብርን በማጠናከር የኢንቨስትመንት እድሎችን እንደሚያሰፋም ተናግረዋል።
ፋና
More Stories
3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ነገ መካሄድ ይጀምራል
የእናትነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 39ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ