May 2, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አራተኛው ዙር የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር ላልተወሰነ ጊዜ ተላለፈ

ለቀጣይ ቅዳሜ በሮም ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው አራተኛው ዙር የኢራን እና አሜሪካ የኑክልየር ድርድር ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

ሁለቱን ወገኖች እያደራደረቻቸው ያለችው ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር ቢን ሃማድ አል-ቡሳይዲ መርሐ ግብሩ የዘገየው ‘በሎጂስቲክ ምክንያቶች ነው’ ቢሉም፣ አንዳንድ ወገኖች በሀራቱ መካከል እየተካረረ በመጣው ውጥረት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አራተኛውን ድርድር እ.አ.አ ለሜይ 3 ቀን 2025 በሮም እንዲካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም አለመሳካቱን ጠቅሰው፣ ቀጣዩን የድርድር ጊዜ በቅርቡ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን የየመኑን ሁቲ መደገፍ እና ኑክልየርን ማበልፀግ በመቀጠሏ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ሊጥሉባት እንደሚችሉ ሲያሳስቡ፣ ኢራን በበኩሏ ኑክልየርን ለሰላማዊ የኃይል ምንጭ ብቻ እያበለፀገች እንደሆነ ገልጻለች፡፡

አሜሪካ በነዳጅ ምርቶቿ ላይ የጣለችው ማዕቀብም ሀገራቱ መተማመን ላይ እንዳይደርሱ ምክንያት እየሆነ መሆኑን ኢራን ጠቅሳለች፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ድርድሩ የዘገየው በኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥያቄ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ፍትሃዊ እና ዘላቂ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸውን የዘገበው አልጀዚራ ነው።