May 1, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሊቨርፑልና ማንቼስተር ዩናይትድ የዋንጫ የበላይነት ፉክክር…

ሚያዝያ 21፣ 2017 በእንግሊዝ ምድር ከፍ ያለ የእግር ኳስ የባላንጣነት ስሜት ከሚስተናገድባቸው የደርቢ ፍልሚያዎች መካከል የላንክሻየር ደርቢ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ማንቼስተር ዩናይትድን ከሊቨርፑል የሚያገናኘው ይህ ደርቢ፡ ሁለቱ ክለቦች ለዋንጫ የበላይነት በሚያደርጉት ፉክክር ሳቢያ ለዘመናት የዘለቀ ነው።

አንደኛው ክለብ በዋንጫ የደመቁ የከፍታ አመታትን ሲያሳልፍ፥ ሌላኛው በውጤት እጦት የዋዠቀበት በርካታ አጋጣሚዎችን አስተናግደዋል።

ለአብነትም በፈረንጆቹ 1970ዎቹና 80ዎቹ ሊቨርፑሎች በ13 የሊጉ ዋንጫዎች ሲደምቁ፥ ማንቼስተር ዩናይትድ በነዛ 20 አመታት አንድም ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ለመሳም አልታደለም ነበር።

በተመሳሳይ ማንቼስተር ዩናይትድ ከ1992/93 እስከ 2012/13 የውድድር አመታት 13 ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ባለክብር ሲሆን፥ ሊቨርፑል አንድም ጊዜ ያን ማሳካት አልቻለም ነበር።

በተለይም ሊቨርፑል ከ1970/71 እስከ 1989/90 ባሉት 20 የውድድር አመታት 13 ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የበላይነት ነበረው።

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ኦልድትራፎርድ ከመድረሳቸው በፊት ሊቨርፑል 18 ጊዜ የሊጉ ባለክብር ሲሆን፥ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ 7 ጊዜ ብቻ ነበር የሊጉ ሻምፒዮን መሆን የቻለው።

ሆኖም ከ1989/90 የውድድር አመት በኋላ ሊቨርፑሎች የሊጉን ዋንጫ ወደ መርሲሳይድ ለመመለስ ሶስት አስርት አመታት ፈጅቶባቸዋል።

በአንጻሩ ሊጉ በፈረንጆቹ 1993 ፕሪሚየር ሊግ የሚለውን ስያሜ ካገኘ ወዲህ ማንቼስተር ዩናይትድ ከስኮቲሹ ታላቅ አሰልጣኝ ጋር 13 ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

እናም ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በፈረንጆቹ 2012/13 የውድድር አመት ከአሰልጣኝነት ራሳቸውን ሲያገልሉ በዩናይትድ ቤተ-መዘክር መደርደሪያ ላይ 20 የሊጉ ዋንጫዎች ተሰድረው ነበር።

ከፈርጉሰን በኋላ ዩናይትድ ከፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መራራቅ ሲጀምር ሊቨርፑል በአንጻሩ ባለፉት 5 አመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን በመሆን ታሪክ መጋራት ችሏል።

ለቀዮቹ መርሲሳይዳውያን አሁን ያሳኩት የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊነት በተለይም በሁለት ምክንያቶች የተለየ ቦታ እንዳለው ይነገራል።

አንዱ ምክንያት ከተቀናቃኞቻቸው ማንቼስተር ዩናይትዶች ጋር ታሪክ መጋራታቸው ሲሆን፥ በሌላ በኩል ከአምስት አመት በፊት በቅጡ ያላጣጣሙትን ድል ዳግመኛ ስላገኙት እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ።

ከ30 አመታት ጥበቃ በኋላ እንዲሁም ሊጉ ፕሪሚየር ሊግ የሚል ስያሜ ካገኘ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ባነሱበት ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት በጋራ ተሰባስበው ድላቸውን ማጣጣም አልቻሉም ነበር።

ሊቨርፑልን ከሶስት አስርታት በኋላ ለአመታት የነገሰበትን የሊግ የበላይነት ዳግም የመለሱትን የርገን ክሎፕን ተክተው አንፊልድ የደረሱት አርኔ ስሎት በመጡበት አመት ለሊቨርፑል ብዙ ትርጉም ያለውን ዋንጫ አስገኝተዋል።

ሊቨርፑሎች በሊጉ አናት ላይ ሆነው አመቱን ሲቋጩ፥ የምንግዜም ተቀናቃኞቻቸው ማንቼስተር ዩናይትዶች በተቃራኒው ከሊጉ ግርጌ ጥቂት ከፍ ብለው ይገኛሉ።

አሁን ሁለቱም ክለቦች 20 ጊዜ ካሳኩት የሊጉ ዋንጫ በተጨማሪ፥ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሊቨርፑል 6 ጊዜ ሲያሸንፍ፥ ማንቼስተር ዩናይትድ ሶስት ጊዜ ማንሳቱን በመጥቀስ ሊቨርፑል የተሻለ መሆኑን የሚገልጹም አሉ።

የኤፍ ኤ ዋንጫን ማንቼስተር ዩናይትድ 13 ጊዜ፣ ሊቨርፑል ደግሞ 8 ጊዜ ሲያሸንፉ፥ በሊግ ካፕ ሊቨርፑል 10 ጊዜ፣ ዩናይትድ 6 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሆነዋል።

እንደ ትልቅ ዋንጫ መቆጠር አለበት ወይስ የለበትም የሚል ክርክር የሚነሳበትን የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫ ዩናይትድ 21 ጊዜ፣ ሊቨርፑል 16 ጊዜ በማንሳት በድምሩ የሀገር ውስጥ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያሳኳቸው ዋንጫዎች በተመሳሳይ 68 ነው።

ምናልባትም በቀጣዮቹ አመታት ሁለቱ ክለቦች ዳግም በዋንጫ የበላይነት ፉክክር ይቀጥሉ ይሆን፥ ወይስ አንዱ ከሌላው ልቆ በበላይነት ይዘልቅ ይሆን የሚለውን ጊዜ ያሳየናል።