March 17, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል በደቡብ ምዕራብ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማሻ አገልግሎት ማዕከል ከከተማው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ።

‎በመድረኩ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችሉ ሀሳቦች በስፋት ተነስተዋል።

‎በምክክር መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አንዱዓለም ጌታቸው እንደ ሀገር የኢኮኖሚ አነቃቂ ከሚባሉት መሠረተ-ልማቶች መካከል ግንባር ቀደሙ የኤሌትሪክ ሀይል አንዱ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎ተቋሙ የፈጠራ አቅሙን በማሳደግ  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት የከተማ አስተዳደሩ እንደሚያግዝ ከንቲባው ገልጸዋል።

‎ተጠቃሚዎችም ለኤሌክትሪክ አገልግሎት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን በንቃት በመከታተል ሊከላከሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎የተቋሙን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በደቡብ ምዕራብ ሪጅን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የፐርፎርማንስ ሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ አባይ በዝርዝር ቀርቧል።

‎230 ኪሎ ቮልት መብራት በከተማው አገልግሎት መስጠት በመጀመሩና በሪጅንም ይሁን በማዕከሉ የሚከናወኑ አገልግሎቶችን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

‎በርካታ ነዋሪዎች በከተማው  ዙር የመብራት ማስፋፍያ ባለመዳረሱ ምክንያት  የመብራት ተጠቃሚ አለመሆን፣ የትራስፎርመር ቁጥር ማነስ፣  ያረጁ  ፖሎችን በጊዜ አለመቀየርና የፖል ዋጋ በየጊዜው መናር  ስለሚስተዋል በርካቶች ከጨለማ እንዳልወጡም አንስተዋል።

‎አልፎ አልፎ ከልክ በላይ ሀይል በሚለቀቅበት ጊዜ ንብረቶች ሲቃጠሉ ኃላፊነት የሚወስድ  አካል አለመኖር በተቋሙ ላይ ቅሬታ ስለሚያስነሳ የቅርብ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ሀሳብ ቀርቧል።

‎የወር ፍጆታ ከፍተኛ መሆን፣ የአከፋፈል ሂደት ላይ በየጊዜው ግንዛቤ አለመስጠት፣ አንዳንድ ባለሙያዎች በቅንነት ያለማገልገል፣  በነባር መስመሮች ላይ የኃይል ማነስ፣ ማዕከሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው የውይይት መድረክ አለማድረግና ሌሎች መሰል ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

‎አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ወደሌሎች አቅራቢያ አከባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ሪጅኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቢሰራ የተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ ስለሚቻል በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራም ሀሳብ ቀርቧል።

‎በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል በደቡብ ምዕራብ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ገብሬ  ከተሳታፊዎች ለቀጣይ ስራቸው አጋዥ ሀሳቦች መነሳታቸውን ገልጸዋል።

በሪጅኑ ስር ከሚገኙ አምስት ሰብ ስቴሽኖች መካከል የማሻው 230 ኪሎ ቮልት መሆኑ ተናግረው ፤ የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላትና ቁጥራቸውን ለማሳደግ ሪጅኑ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

‎በተለይ ከማስፋፍያ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና ግንዛቤን ከማስጨበጥ አንጻር ለተነሱ ጥያቄዎች በአሰራር ስርዓት ላይ በቀጣይ ከደንበኞች፣ ከከተማ አስተዳደሩና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምላሽ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

‎በሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቋሙ አሰራርና መመሪያ መሰረት ምላሽ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን ፤ በቀጣይ የደንበኞቹን ፍላጎት መነሻ በማድረግ የነበሩ የግንዛቤ ጥያቄዎችና  ለሌሎች  ተገቢው ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል በደቡብ ምዕራብ ሪጅንና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግለዎች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።