March 10, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ በሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ውስጥ በመሆን በአሳታፊ ደን አስተዳደር ማህበር የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ።

ማሻ፤ መጋቢት 1/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ፕሮጀክቱ በወረዳው እያከናወነ ያለውን ተግባር ከፌዴራልና ክልል እንዲሁም ከዞንና ወረዳ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ምልከታ በማድረግ ቀጣይ የደን ሀብት ጠብቆ ማቆየት በሚያስችሉ ጉዳዩች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።

በማሻ ወረዳ የሚገኙና በሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም የታቀፋ ሰላም እና ወሎ ደን ጥበቃና ደን ውጤቶች ግብይት ሀላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር አባላት እንደገለፁት በፕሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።

በዚህም በማህበር ተደራጅተው የደን ሀብት ከመጠበቅ በተጨማሪ በድለባ፣እርባታና ለሎች የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቁመዋል።

አሁንም አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን የደን ሀብት በመጠበቅ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰሩ የገለፁት አባላት የመንገድና ለሎች ችግሮችን የሚመለከተው አካል እንድፈታ ጠይቀዋል ።

የማሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍ አዳሾ በበኩላቸው የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የማህበሩ አባላት ያነሱትን ችግር ለመቅረፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።

በወረዳው ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኝ የደን ሀብት በሬድ ፕላስ ፕሮጀክት በታቀፋ የአሳታፊ ደን ማህበራት እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ ደን ከመጠበቅ በተጨማሪ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውንና ይህን ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።

የሸካ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አረጋሀኝ አለሙ በበኩላቸው መምሪያው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰሩ ገልጸዋል ።

የሸካ ዞን የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ታደሰ ሾበኖ በበኩላቸው በዞኑ ባሉት ሶስት ወረዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ በበኩላቸው የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት በክልል ደረጃ 38 ወረዳዎች ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከ250 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

የሸካቾ ብሔረሰብ የደን አጠባበቅ ስርዓት ለሎችም ተሞክሮ እንደሚሆን የገለፁት ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያና የዘላቂ ልማት አማካሪ አቶ ነፃነት ደነቀ የህብረተሰቡን የደን አጠባበቅ ስርዓት ለማስቀጠልና ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል ።

ከኢትዮጵያ ደን ልማት ፣ ከፌዴራል የገንዘብ ሚንስቴር እንዲሁም ከክልልና ዞን የተገኙ ከፍተኛ የዘርፉ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በቦታው ተገኝተው ማህበሩ እያከናወነ ያለውን የስራ እንቅስቃሴና በወረዳው የሚገኘውን የደን ሀብት ምልከታ ምልከታ አድርገዋል።