March 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ሚና ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለጸ

ማሻ፤ የካቲት 25/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8)የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የ6ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቴፒ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩም በግማሽ ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖች እንዲቀጥሉና የታዩ ክፍተቶች በቀሪው የበጀት ዓመት እንዲታረሙ አቅጣጫ ተቀምጧል።

መድረኩን የመሩት ​የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን የፍትህ ተደራሽነትን ማረጋገጥና አሰራርን በቴክኖሎጂ ማዘመን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

​የህዝቡን ባህልና እሴት መሰረት ያደረጉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በሁሉም መዋቅሮች ላይ በስፋት ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የፍትህ አገልግሎቱ ቀልጣፋና ግልጽነት የተሞላበት እንዲሆን ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ መዘመን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

​በፍትህ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የጥምር ፍትህ ጉባኤ፣ ውይይትና ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ህብረተሰቡ ባሉበት አካባቢ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የተዘዋዋሪ ችሎት አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

​የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ አስረስ በበኩላቸው የፍትህ አገልግሎቱ ቀልጣፋና ተዓማኒ እንዲሆን አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የታገዙ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የፍትህ ስርዓቱ የህዝብ አመኔታ እንዲኖረው ማስረጃዎች በጥንቃቄ ሊመረመሩና ባለሙያዎች ከሙስና ተግባር ሊጸዱ እንደሚገባ በጥብቅ አሳስበዋል።

የዳኞችን የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

​የባህል ፍርድ ቤቶች ውጤታማነታቸው እንዲረጋገጥ የፍትህ አካላት አስፈላጊውን እውቅና በመስጠትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን ሊደግፏቸው እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

​የውይይቱ ተሳታፊዎች የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ግጭቶችን በእርቅ ለመፍታት ያላቸውን ሚና በማድነቅ፣ ተቋማቱ በበጀትና በሎጅስቲክስ ሊደገፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የዳኞችና የባለሙያዎች እጥረት፣የቢሮ ቁሳቁስና የበጀት ውስንነት፣ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ ጥያቄዎችን  በዋናነት አንስተዋል። ዘገባው የዞኑ መ/ኮ ነው።