March 2, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ ሰራተኞች የአድዋን ድል በዓል፣ ዋናው ጣቢያ የተመሰረተበን 21ኛ ዓመት እና ቅርንጫፉ ስርጭት የጀመረበትን 2ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

ማሻ፤ የካቲት 23/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ሚዲያ የማሳወቅ፣ የማዝናናትና የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ አይነተኛ ሚና ያለው መሳሪያ በመሆኑ አባቶች ያወረሱንን አርበኝነት በተሰማራበት የሙያ መስክ ለመድገም እንደሚሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ጎዱ ከተቋቋመ 21 የስኬት ዓመታትን የዘለቀው ድርጅቱ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት 11ኛውን ቅርንጫፍ ማሻ ላይ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል ብለዋል።

የካቲት 23 በሀገራችን ታሪካዊና የጥቁር ህዝቦች የድል በዓል በሚከበርበት ዕለትጣቢያችን ድርብ በዓል እያከበረ መሆኑን ተከትሎ እለቱን አይረሴ ተግባራት በማከናወን ለማክበር የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ መመረጡንም አቶ ታምሩ አክለዋል።

አባቶች ዘመን አይሽሬ ገድል ፈጽመው ያጸኗትን ሀገር ለማስቀጠል እንደ ሚዲያ የተጣለብንን ሀገራዊ አደራ ለመወጣት በትጋት ለመስራት ቃላችንን የምናድስበት አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል።

በሸክሸኮ ዋሻና ፏፏቴ ጉብኝት ላይ ያገኘናቸው የድርጅቱ ሰራተኞች በቅርብ ርቀት የነበረውን ውብ ተፈጥሮ ዛሬ ከዚህ ታሪክ ጋር አጣምረን መጎብኘታችን ልዩ ስሜት ፈጥሮብናል ብለዋል።

ሌሎች መሰል ተቋማትም የተለያዩ ክስተቶችን እና ኩኔቶችን በዚህ መልኩ ቢያከብሩ መልካም ግንኙነት የመፍጠር እና የስራ ተነሳሽነትን ያሳድጋል ብለዋል።