ማሻ፤ የካቲት 23/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) አስተማማኝና ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት መብታችን የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ጉዳይ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ዓድዋን ስናስብ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሉዓላዊነት የከፈሉትን ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ሰፊ ራዕይ ጭምር ነው፡፡
የዛሬው የዓድዋ በዓል ትርጉም ነጻነትን በብልጽግና ማስዋብና ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ አኩሪ ተግባር መፈጸምና ማስተላለፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዓድዋ ድል ማግስት የዲፕሎማሲው ትግል አንዱ ማጠንጠኛ ኢትዮጵያ ከዓለም የምትገናኝበትን የባሕር በር እና የወደብ ባለቤትነት የማረጋገጥ ጉዳይ ዋነኛው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ዛሬም እኛ የምንሻው እንግዳ ጉዳይ ሳይሆን ይህንኑ የታሪክ መንገድ እና ፈለግ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አስተማማኝ እና ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት መብታችን የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይለጠል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ጥያቄውን ዝንታለም ልንሸሸው ብንሞክር እንኳን መቼም ቢሆን ከእኛ ሊነጠል የማይችል ሕያው ሐቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር ያደረግነው የዘመናት ተጋድሎ ሲታይ ታሪክ ለኢትዮጵያ በጎና መልካም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በአልፎ ሒያጅና በሰሞንተኛ የፖለቲካ ርዕዮት ስሌት ታሪካችንና ስትራቴጂካዊ መልሕቃችን መስዋዕት እንድናደርግ ተገደናል ነው ያሉት፡፡
ስለሆነም ዓድዋ የሚያስተምረን በመሰል ጉዳዮች ላይ የምንወስደው ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ከታሪክ ትክክለኛ ጎን መቆም መቻል እንዳለብን ነው ብለዋል፡፡
ትናንት በዓድዋ አውድማ የተገኘው ወታደራዊ ድል ዛሬ በኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ድል ካልታጀበ ትርጉሙ ምልዑ እንደማይሆን አብራርተዋል፡፡
የሀገራችን የኢኮኖሚ ጥማት የሚረካውና የ120 ሚሊየን በላይ ሕዝቦች እጣ ፈንታ ብሩህ የሚሆነው ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ ግርግም ወይም በየብስ እግረ ሙቅ አለመታሰሯን ስናረጋግጥ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ይህን የምንለውም እንደ ዓድዋ ጀግኖች ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን የእድገት ትንሳዔ ለማብሰር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
መንገዳችንና መሻታችን የጉዟችን ዳራም ሰላማዊ እና አብሮ ተባብሮ ማደግ ነው ፤ የባሕር በር ጥያቄያችንም የታሪክና የፍትሕ ጥያቄ እንዲሁም የትውልድ ሕልውና ጉዳይ አድርጎ መረዳት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ መንፈስ የሚጠየፈው ቅጥረኝነትን ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ ÷ ተገዥነት፣ ቅጥረኝነትና ባንዳነት ያሳዝንና ያስተዛዝብ እንደሆን እንጂ ኢትዮጵያን አሸንፎ አያውቅም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
More Stories
ትውልዱ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፦ አርበኞችና ስካውቶች
ሰርጌይ ላቭሮቭ ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ ሰራተኞች የአድዋን ድል በዓል፣ ዋናው ጣቢያ የተመሰረተበን 21ኛ ዓመት እና ቅርንጫፉ ስርጭት የጀመረበትን 2ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።