March 2, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ትውልዱ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፦ አርበኞችና ስካውቶች

ማሻ፤ የካቲት 23/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለ130ኛው የዓድዋ የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር እና የአዲስ አበባ ስካውት ማኅበር አባላት በተቋሙ የተዘጋጀውን ዲጂታል ኤግዚቢሽን መጎብኘታቸውን አስታውቋል።

በጉብኝቱ ወቅት አርበኞቹና የስካውት አባላቱ እንደገለጹት፣ የአሁኑ ትውልድ የአድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት ይኖርበታል።

የሀገር ሰላምና ደኅንነት በትውልዶች ቅብብል የሚረጋገጥ መሆኑን የጠቀሱት ጎብኚዎቹ፣ የስለላ ጥበብ ለዓድዋ ድል ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በመረጃና ደኅንነት ተቋሙ ውስጥ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት ለመከላከል የሚያስችል ብቁ አቅም መፈጠሩን በተግባር እንዳሳዩአቸው ገልጸዋል።

ይህም ተቋሙ ላይ ያላቸው መተማመን ከፍ እንዲል ማድረጉን ጠቁመዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ስካውት ማኅበር አባል የሆኑ ተማሪዎች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አርበኞች ስለከፈሉት መስዋዕትነትና ስላስረከቧቸው ነፃ ሀገር ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የተጣለባቸውን የሀገር አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በቁርጠኝነት ተናግረዋል።

አርበኞቹና የስካውት አባላቱ አድዋ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፀንታ እንድትቆም ያደረገው አበርክቶ ዘላቂ መሆኑን አውስተው፣ በወቅቱ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ዜጎች ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት መቆማቸው ለድሉ ዋነኛ መሠረት እንደነበረና ይህም ለዛሬው ትውልድ ታላቅ ትምህርት የሚሰጥ እሴት መሆኑን መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ያገኛሉ !