February 25, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

130ኛውን የዓድዋ ድል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ

ማሻ፤ የካቲት 17/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የዓድዋ ድል በዓል መከበር የኢትዮጵያዊነት የጥንካሬና የፅናት መሠረት ዳግም የሚታደስበት፤ ለሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት የገባነውን ቃል ኪዳን የምናጸናበት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አከባበር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ የድል በዓሉን “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተጠናቅቋል ብለዋል።

130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ስናከብር የኢትዮጵያዊነትን የጥንካሬና የፅናት መሠረት ዳግም የምናድስበት፣ ለሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት የገባነውን ቃል ኪዳን የምናጸናበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች ላይ ዘር፣ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለያቸው ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር በኅብረት የቆሙበትና ተጋድሎ የፈጸሙበት የጋራ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው መሪ ሀሳብ ትናንት በጀግኖች ደምና አጥንት የተጠበቀችውን ሀገር ዛሬ በዘላቂ ሰላምና በልማት ወደ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ከፍታ ለማሻገር ያለንን ፅኑ ቁርጠኝነት እንደሚገልጽም አብራርተዋል።

ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትም የዓድዋን የጀግንነት ውርስ በመሰነቅ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ወደ ብሩህ አድማስ የምናደርገውን ጉዞ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። በዓሉ መላው ኢትዮጵያውያን የነገውን ብሩህ አድማስ በጋራ የሚያልሙበት እንደሚሆንም ሚኒስትሯ መግለጻቸው ተዘግቧል