February 25, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን መገንባት የሚያስችል ወሳኝ አጀንዳ ነው – አምባሳደር ሶፊ ፍሮም- ኤመስበርገር

ማሻ፤ የካቲት 17/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላምን መገንባት የሚያስችል ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም- ኤመስበርገር ገለጹ።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም- ኤመስበርገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያና አውሮፓ ሕብረት መካከል በሁሉም ዘርፍ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር መኖሩን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረትም የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን፣ ታዳሽ ኃይል፣ ግብርና፣ የትምህርትና ሥልጠና የሰው ሃብት ልማት ስራዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በጥቅምት ወር በብራስልስ በነበራቸው ቆይታም ከአውሮፓ ሕብረት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የነበራቸው ውይይት ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ የቡድን-20 ሀገራት ስብሰባ ላይ ከሕብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ጋር በዲፕሎማሲ ትብብር ጉዳዮች መምከራቸውን አስታውሰዋል።

ይህም የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት 50 ዓመታት ያሳለፈውን የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ወደላቀ የትብብር ምዕራፍ በማሸጋገር አጋርነትን እያጠናከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ሃያ ሁለት የሕብረቱ አባል ሀገራት በተለያዩ የልማት መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር እያሰፉ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በቀጣይም በሁሉም መስክ የኢትዮ-አውሮፓ ሕብረትን የዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችሉ ወሳኝ አጀንዳዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም አጀንዳዎች ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳም የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ አመላካከቶችን በጋራ መድረክ በመምከር መግባባትን ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በኢትዮጵያዊያን ባለቤትነት የሚመራ መሆኑም ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል መድረክ ለማመቻቸት ትርጉም እንደሚሰጠው አንስተዋል።

የሀገራዊ ምክክር መድረክ የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሰለጠነ የንግግር መድረክ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ሥርዓትና ልምድ መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ምክክር የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሯ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም ብሔራዊ መግባባትን መገንባት የሚያስችል ወሳኝ አጀንዳ ነው ብለዋል።

#ENA