ማሻ፤ የካቲት 16/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በተግባር የተደገፈ የመደመር እሳቤ ለተጨባጭ የኢኮኖሚ እመርታዊ ለውጥ ዋነኛ መንገድ በመሆኑ ለቀጣይ ዓመታት አጠቃላይ የኢኮኖሚ አቅምን ከዕዳ ወደ ምንዳ ለማሻገር እየተሠራ ይገኛል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ”ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና ምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ብልጽግና በቀጣዩ 7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በመወዳደር እንደሀገር የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተጋ ያለ ሁነኛ ፓርቲ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
የደቡብ ምዕራብ ክልል እጣ ፋንታቸው የተጋመደና የተሳሰረ ህዝቦች በጋራ ተሳስበው የሚኖሩበት ክልል በመሆኑ አንዳችን ላንዳችን ደጋፊና መከታ በመሆን ብልጽግናችንን ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከባህር በር ርቃ በመቆየቷ ምክንያት ህልውናዋ ፈተና ውስጥ እንዳይገባ ጂኦ ፖለቲካዊ እውነታን መሠረት በማድረግ ሀገሪቱን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ ብልጽግና እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ስለተገኙ ውጤቶችና በቀጣይ 5 ዓመታት ለማከናወን ስለታቀዱ ወሳኝ ጉዳዮች ይፋ ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫን በአብላጫ ድምጽ በማሸነፍ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ዘላቂ ማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች የተቀመጡ ውጥኖችን እውን ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተጨማሪ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ሌላኛው ወሳኝ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም የመገንባት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተግባር የተደገፈ የመደመር እሳቤ ለተጨባጭ የኢኮኖሚ እመርታዊ ለውጥ ዋነኛ መንገድ በመሆኑ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አቅምን ከዕዳ ወደ ምንዳ ለማሻገር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ብልጽግና ቃልን በተግባር ህልምን ወደ እውን ማሸጋገር የቻለ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ተምሳሌት በመሆኑ ለቀጣይ የተያዘ ትልቅ ራዕይን እውን ለማድረግ በቀጣይ ምርጫ ዜጎች ብልጽግናን እንዲመርጡ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በመጪው ወርሃ ግንቦት ልታካሂድ ባቀደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና እንደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የሀገሪቱንና የዜጎቿን ተጨባጭ ፍላጎት ለማሟላት ታላቅ ራዕይ ይዞ በምርጫው ለመወዳደር ዝግጅቱን ከማጠናቀቁም በላይ ምርጫው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የዴሞክራሲ ትልም ትልቅ አብነት እንዲሆን ጭምር የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ በወቅቱ ተመላክቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብዝሃ ማንነት ተምሳሌት እንደመኑ ሕብረ ብሔራዊነት በክልሉ ሥር እንዲሰድና ዜጎች ጠንካራ አንድነትን አዳብረው መጪውን እንዲያልሙ ፓርቲው እየሠራ እንደሚገኝም ተነግሯል።
በመርሃ ግብሩ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስትና ፓርቲ አመራሮች፣ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችም የመድረኩ ድምቀት ነበሩ
More Stories
የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደር ምክክር
ዋሽግተን-ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕን የቀረጥ ጭማሪ ደንብ ዉድቅ አደረገ
ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ 2.6 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘች