ማሻ፤ የካቲት 13/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ አዘጋጅነት ለዞን፣ ለከተማና ለወረዳ የገቢ ተቋማት ፈፃሚዎች በሥነ-ምግባር እና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያተኮረ የመገምገሚያ ኦሬንቴሽን መድረክ በቴፒ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት በላይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የገቢ ተቋሙ የዞኑንና የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም፣ አሁንም በየደረጃው በሚታዩ ችግሮች ምክንያት ያለውን አቅም (ፖቴንሻል) ሙሉ በሙሉ መጠቀም አልተቻለም።
በአመራሩና በፈፃሚው ዘንድ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ክፍተቶችን በመቅረፍ ውጤታማ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋት የመድረኩ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ገለጻ፤ በክልሉ በየዓመቱ ከ4 ቢሊዮን እስከ 18 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ አቅም ቢኖርም፣ አሁን ላይ እየተሰበሰበ ያለው ግን ከዚህ በታች ነው።
በአሁኑ ወቅት ክልሉ የራሱን ወጪ እስከ 64% መሸፈን የቻለ ሲሆን፣ ቀሪውን 36% ለመሸፈን የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግና ለዚህም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው በቀለ በበኩላቸው፤ መድረኩ በየተቋማቱ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባርና አጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር ከተከሰቱ ችግሮች በመውጣት፣ የዞኑን የልማት ፍላጎት ሊደግፍ የሚችል ቀልጣፋ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማ፣ የዞኑ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙን ጨምሮ የመንግሥት ተጠሪዎች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ተገኝተዋል። ዘገባው የዞኑ መ/ኮ ነው
More Stories
ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ትርጉም አልባ ያደርገዋል አለች
የሸካ ህዝቦች ልማት ማህበር የጀመረው የሰንበት ገቢያ በበዓል ወቅት ከሚፈጠረው የዋጋ ንረት ታድጎናል ሲሉ የሸካ ዞን ማሻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በማረፋቸው የተሰማኝን ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ።