February 19, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የአደይ ፕሮግራም በክልሉ 4078 ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከ70 ሚልዮን ብር በላይ መድቦ ወደ ተግባር እየገባ  ይገኛል_ዶ/ር ዐብይ አንዴሞ

ማሻ፤ የካቲት 12/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአዴይ ፕሮግራም ስትሪንግና ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት የጋራ መድረክ በታርጫ ከተማ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙ የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊና የ”አደይ” ፕሮግራም የስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ዐብይ አንዴሞ የአዴይ ፕሮግራም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በፕሮግራሙ በታቀፉ ዞኖች 4078 ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከ70 ሚልዮን ብር በላይ መድቦ ወደ ተግባር እየገባ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚነት የሁሉም የባለድርሻ አካላት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት ዶ/ር ዐብይ ስራ አጥ ወጣቶችን በፍላጎትና እንደየአካባቢ አስቻይ ሁኔታዎች በኢንተርፕይዝ በማደራጀት ውጤታማ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል።

ለፕሮግራሙ ውጤታማነት የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርና ሀላፊነት እጅግ ወሳኝ እንሆነ ተጠቅሷል።

በግብርና ትራንሰፎርሜሽን ኢንሰቲትዩት (አትአይ) የደቡብ ማስተባበሪያ ስራ አሰኪያጅ የሆኑት አቶ ግርማሜ ጋሩማ በበኩላቸው ስራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች በክላስተር ማደራጀት ለተግባሩ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከስልጠናና ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

ፕሮግራሙ 80% ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የተገለፀ ሲሆን ለአደረጃጀቱ ፍላጎትና አዋጪ ዘርፎች ትኩረት እንደሚደረጉ ተብራርቷል።

መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አፅንኦት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ የገለፁ የምክትል ርዕስ መስተዳድር አማካሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ ናቸው።

አቶ ዮሐንስ አክለውም ወጣቶችን በማነቃነቅ፣ የስነ ልቦና ውቅር በማስተካከል፣ ስልጠና በመስጠትና ሀብት በመመደብ በተገቢው ወደ ስራ ማሰማራት ከሁሉም የባለድርሻ አካላት በተግባር የሚጠበቅ ሀላፊነት እንደሆነም አንስተዋል።

ምልመላና መረጣ ከዩኒቨርስቲ፣ ከኮሌጆችና ከቴክኒክ ሙያ ተቋማት ተመርቀው ስራ ያጡ ወጣቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል።

ወጣቶች በሚደራጁባቸው የስራ መስኮች አስፈላጊው ስልጠና እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በተገቢው እንደሚሰጥም ተብራርቷል።

በስልጠናው በክልሉ በፕሮግራሙ ከታቀፉ ከ5 ዞኖችና ከስድስት ወረዳዎች የተወጣጡ የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል