ማሻ፤ የካቲት 11/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ኃይሌ ገሪማ በጀርመን መዲና በርሊን ትናንት ማክሰኞ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል (Berlinale) ላይ ለፊልም ጥበብ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች የሚሰጠው «የበርሊን ካሜራ» (Berlinale Camera) የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ኃይሌ ገሪማ በአፍሪካ ታሪክ፣ በቅኝ አገዛዝ፣ በማንነት እና በማኅበራዊ ፍትህ ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ዳይሬክተር፣ አዘጋጅ እና መምህር ናቸው።
ለበርካታ አስርት ዓመታት በአሜሪካ በሚገኘው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮፌሰር በመሆን በርካታ ወጣት የፊልም ባለሙያዎችን ማፍራታቸው የሚነገርላቸው ኃይሌ ገሪማ በተለይም በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦችን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ተሞክሮዎች የሚዘክሩ «ሰንኮፋ» እና «ጤዛ» በተሰኙ ፊልሞቻቸው አድናቆት አትርፈዋል።
በርሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ዴልፊ ፊልም ፓላስት በተካሄደ ልዩ የፊልም ማሳያ መርኃ ግብር ላይ ፕሮፌሰር ኃይሌ «ጥቁር አንበሶች ፤ የሮማ ተኩላዎች» (Black Lions – Roman Wolves) የተሰኘውን አዲሱን የፊልም ፕሮጀክታቸውን አስተዋውቀዋል።
አዲሱ የፊልም ሥራቸው ጣሊያን ቅኝ ለመግዛት ያደረገችው ሙከራ በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ፣ ሙከራውን ለማክሸፍ የተደረገውን ተጋድሎ እና የታሪክ ትውስታን የሚዳስስ እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ዓለም አቀፍ ክብር ያጎናጸፋቸው ሽልማት የተበረከተላቸው ለነጻ የሲኒማ ጥበብ ላላቸው የዕድሜ ልክ ቁርጠኝነት፣ ታሪክን በፊልም የመተረክ ብቃታቸው፣ እንዲሁም የአፍሪካውያንን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲሰማ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት እውቅና ለመስጠት ነው ተብሏል። ሽልማቱ ፕሮፌሰር ኃይሌ ከተጎናጸፉት ክብር ባሻገር ለኢትዮጵያ እና ለመላው አፍሪካ የፊልም ኢንዱስትሪ ትልቅ ኩራት የሚሆን ነው። በተጨማሪም ዓለምን የሚያስተምር እና የሚያነቃቃውን የኃይሌ ገሪማን የጥበብ ጉዞ በድምቀት የዘከረ ሆኗል።
#DW AMHARIC
More Stories
ሶማሊያ በአሜሪካ ድጋፍ በአል-ሸባብ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ማጠናከሯ ተገለጸ።
ሦስት አዳዲስ የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማሪፊያዎች በቅርቡ አገልግሎት ይጀምራሉ
በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ(ፕላስቲክ) አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ዙሪያ በቴፒ ከተማ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ።