February 18, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሶማሊያ በአሜሪካ ድጋፍ በአል-ሸባብ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ማጠናከሯ ተገለጸ።

ማሻ፤ የካቲት 11/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ሶማሊያ በአሜሪካ ድጋፍ በሚፈጸሙ የአየር ድብደባዎች እና በቅርቡ ተጠናክረው በቀጠሉ የምድር ወታደራዊ ዘመቻዎች ከአል-ሸባብ ጋር ለዓመታት ስታደርግ የነበረውን ጦርነት መልክ እየቀየረው መምጣቱን የሀገሪቱ መንግሥት አስታውቋል። የሶማሊያ መንግሥት እንዳለው ቀደም ሲል በጽንፈኞች ቁጥጥር ስር የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅ ችሏል። በተጨማሪም በዘመቻው የቡድኑን አመራር ጨምሮ የቦምብ ማምረቻ እና ማስተላለ,ፊያ መረቦችን ኢላማ ማድረጉን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሷል።

የሶማሊያ መንግሥት ከአልሸባብ አንጻር አስመዘገብኩ ያለው ወታደራዊ ድል የተሰማው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በሂደት ከሀገሪቱ እየወጡ ባለበት እና ሶማሊያ የራሷን የጸጥታ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመረከብ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ላይ ነው ተብሏል።

ለዓመታት የአል-ሸባብ ይዞታ የነበሩት የታችኛው ሸቤሌ፣ ሂራን እና ጁባላንድ ግዛቶች አሁን በመንግሥት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ኦማር አሊ አብዲን ጠቅሶ አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። በዘመቻው በተለይ በአሜሪካ የሰለጠነው “«ዳናብ» የተሰኘው የሶማሊያ ልዩ ኃይል በከፈተው ዘመቻ በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውንና ተሽከርካሪዎች መማረካቸውን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የአሜሪካው የአፍሪካ ዕዝ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ (AFRICOM) ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የአል-ሸባብ የስልጠና ማዕከላትና የፈንጂ ማምረቻዎችን ዒላማ ያደረገ አየር ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል። የጸጥታ ተንታኞች እንደሚሉት ቀደም ሲል በምድር ውጊያ ተመጣጣኝ አቅም የነበራቸው ተፋላሚዎቹ አሁን መንግሥት በድሮን ክትትል የታገዘ የአየር የበላይነት መውሰዱ የዉግያ ሚዛኑ እንዲያጋድልለት ረድቶታል ነው የተባለው።

የሶማሊያ መንግሥት ምንም እንኳን ወታደራዊ ድሎች ማስመዝገቡን ቢገልጽም አል-ሸባብ አሁንም በመዲናዋ ሞቃዲሾ ቦምቦችን የማፈንዳት አቅም እንዳለው ይነገራል። በተጨማሪም የመንግሥት ጦር በለቀቃቸው አካባቢዎች ታጣቂዎቹ ተመልሰው እንዳይገቡ ጠንካራ አስተዳደራዊ አገልግሎት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ሶማሊያ ዓመታትን ካስቆጠረው ጦርነት በተጨማሪ ከድርቅ እና የግዛት አንድነቷን ከሚፈታተኑ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ጋር እየታገለች ትገኛለች።

#DW Amharic