February 16, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በአፍሪካ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የፓን አፍሪካ የኢኖቬሽን ኮሪደር መፍጠር ይገባል፡- ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ

ማሻ፤ የካቲት 9/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በአፍሪካ የወጣቶችን ክህሎት በማጠናከር ዘላቂ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የፓን አፍሪካ የኢኖቬሽን ኮሪደር መፍጠር ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም 2026 በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በመድረኩ በአፍሪካ 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች መሆኑን ጠቅሰው፣ አህጉሪቱ ይህንን የሰው ኃይል ታሳቢ ያደረገ የክህሎት ግንባታና የኢኖቬሽን ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባት ገልጸዋል።

የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ስትራቴጂ እና በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።

ፎረሙ “የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ሥራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

መንግሥታት፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ በአፍሪካ እሴት በሚጨምሩ ተግባራት ላይ እንዲሰሩ፣ ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እና ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት እንዲሰጥ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጋራ እና በብርቱ እንዲሰሩ በፎረሙ ጥሪ ቀርቧል።

በመድረኩ የመንግሥት ተቋማት አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ኢቢሲ ዘግቧል