ማሻ፤ የካቲት 8/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በጤናው ዘርፍ የዜጎችን ማኅበራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑም ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በተላይ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የ2018 ዓ/ም የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አፈጻጸም በተሻለ ሁኔታ መፈጸሙን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የነባር አባላት ዕድሳት 90 ከመቶ መድረሱን የገለጹት ኃላፊው ፣አዲስ አባላት ምጣኔ 30 ከመቶ መድረሱንና አጠቃላይ የ2018 ዓ.ም ምጣኔ 74.1 ከመቶ መፈጸሙን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሁለት ወራት 466 ሚሊዮን ብር በላይ ከነባር አባል ዕድሳትና ከአዲስ አባላት መዋጮ መሰብሰቡን የገለጹት አቶ ኢብራሂም፣ በክልሉ በጤናው ዘርፍ የዜጎችን ማኅበራዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።
የአገልግሎትና አባላት ምጣኔውም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር መሻሻል ማሳየቱን የጠቆሙት ኃላፊው በበጀት ዓመቱ በባለድርሻ አካላት ቅንጅት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በክልሉ 419ሺህ 418 አባወራዎች የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ይህም በህዝብ ደረጃ ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አሰረድተዋል።
ከዚህ ቀድም ከአግልግሎት አሰጣጥ ጋር በስፋት ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በጤና ተቋማት ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣በዚህም በህዝብ ዘንድ አመኔታ ማደጉን ገልጸዋል።
በክልሉ 18 የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶች መከፈታቸውን የገለጹት አቶ ኢብራሂም ከዚህ በተጨማሪ በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት በማሻሻል ይነሱ የነበሩ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት መቻሉን አስረድተዋል።
ከሰበሰበው የአባላት መዋጮ ከ277 ሚሊዮን ብር በላይ ለመድኃኒት ግዥ መዋሉን የጠቆሙት ኃላፊው የመድኃኒት አቅርቦት፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ተግባራት ላይ ትርጉም ያለው መሻሻል አምጥቷል ብለዋል።
በእነዚህ በሌሎችም መሠረታዊ መሻሻሎች የኅብረተሰቡ እርካታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን የገለጹት ኃላፊው በቀጣይም አግልግሎቱን ለማሻሻል በተከታታይነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ 68.8 ሚሊዮን ብር ለአባላት የሪፈራል ህክምና መከፈሉን ያነሱት አቶ ኢብራሂም ፍትሀዊ የጤና አግልግሎት ተደራሽነት በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የማህበራዊ ጤና ኢንሹራንስ (Social Health Insurance ) ለጤና ባለሙያዎችና ለጤና መዋቅር የአስተዳደር ሰራተኞች የፌዴራል መንግስት በፈቀደው መሠረት 83 ከመቶ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የጤና መዋቅር ሰራተኞች አስፈላጊው የምዝገባ ስርዓት በመፈፀም የማህበራዊ ጤና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል።
ለመተዘገበው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና አግልግሎት መሻሻል የባለድርሻ አካላት የላቀ ተሳትፎ፣ ድጋፍና ትብብር የጎላ ድርሻ እንደነበረ የገለጹት ኃላፊው፣ በቀጣይም የአግልግሎት አሰጣጡን ለመሻሻል በሚደረገው ተከታታይ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
More Stories
አፍሪካ የራሷን የክትባት እና የሕክምና ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችላትን ጉዞ መጀመሯ ወሳኝ እርምጃ ነው
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ
በክልሉ ሸካ ዞን የኪ ወረዳ ሠላም በር ቀበሌ ከሠላም በርመንደራሻዲካይ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባው 3 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ