February 12, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ሙከራ ሥርጭት ጀመረ

ማሻ፤ የካቲት 05/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ሙከራ ሥርጭቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ዶ/ር) በማስጀመሪያው ወቅት እንደገለጹት፤ ሚዲያ ኔትዎርኩ በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት፣ የማህበረሰቡ ብዝሃ ማንነት፣ ቋንቋና ወግ ከሀገር አልፎ በዓለም ደረጃ እንዲተዋወቁ በትኩረት እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከክልላዊ አንድነት ባሻገር ህብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮችን የሚዲያና ጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነምግባር በተላበስ መልኩ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት ለማኅበረሰቡ በጥራትና በታማኝነት ሊያደርስ ይገባሎም ብለዋል።

በዚህም በክልሉ የሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሥራዎችን ወደ ህዝቡ ከማድረስ አልፎ የህዝብ ድምጽ በመሆን ማገልገል እንዳለባቸውም አስረድተው ሚዲያው ጠንካራና ተመራጭ ለመሆን የጀመረውን ጥረት የክልሉ መንግስት ይደግፋልም ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ የክልሉ ሚዲያ ኔትወርክ እንዲቋቋም በክልሉ ምክር ቤት ጸድቀው ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ምኮር ቤቱ የድጋፍና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ይህን በቀጣይነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሚዲያ በህዝብ እና መንግስት መካከል ድልድል በመሆን የሚያገለግል ትልቅ አውድ እንደሆነም የተናገሩት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊና የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ የሺዋስ ዓለሙ ናቸው።

የሥራ አመራር ቦርዱም በክልሉ ምክር ቤትና መንግስት ኃላፊነት ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት፣ተሞክሮዎችን በመቀመርና የተሻለ ሚዲያ ሆኖ እንዲወጣ  ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ሚዲያ ኔትዎርክ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ መከሪያ እንዳሉት፤ ሚዲያ ኔትዎርኩ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቀው ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ተቋሙን በሰውና በቁሳቁስ ማደራጀት ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ከማድረስ ባሻገር በቴሌቪዥን መስኮት መረጃዎችን  ለማድረስ ዝግጅቱን ጨርሶ ሙከራ ስርጭት ጀምሯል።

ኔትወርኩ ሥርጭቱን ለመጀመር የሚያስችለውን ሕጋዊ ፈቃድና ዕውቅና ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ማግኘቱንም አስታውቀዋል።

የሙከራ ሥርጭቱ Ethio_sat NSS 12 57° East፣ Frequency 11605 MHz፣ Symbol Rate 45000፣ Polarization Horizontal በመጠቀም መከታተል እንደሚቻል የገለጹት ስራ አስኪያጁ ለስድስት ወራት የሙከራ ሥርጭት ካካሄደ በኋላ መደበኛ የቴሌቪዥን ሥርጭቱን እንደሚጀምር ነው የገለጹት።

ኔትወርኩ በዛሬው ቀን የሚካሄደውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ መረጃዎችን ለተመልካች የሚያደርስ ይሆናል።

በማስጀመሪያው ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።