February 9, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የዲዚ ብሔረሰብ ማህበራዊ ድልብ ሀብቶችን ለክልላዊ አንድነትና ልማት ማዋል ይገባል፦ ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ማሻ፤ የካቲት 2/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት የዲዚ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ”ከይ ቢያርግ በዓል  በማጂ ከተማ ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበዓሉ ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው፤ የብሔረሰቡ ማህበራዊ ድልብ ሀብቶች በተገቢው በማልማትና በመንከባከብ ለክልላዊ አንድነትና ዘላቂ ልማት ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ክልሉ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የዲዚ ብሔረሰብ ከእነዚህ መካከል በረጅም ዘመናት የተስተናገደ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና ባህላዊ የማህበረሰብ አስተዳደር ሥርዓት ያለው ማህበረሰብ መሆኑን አመልክተዋል።

እነዚህ ማህበራዊ ድልብ ሀብቶች የማህበረሰቡ ልዩ መገለጫና ኩራት ብቻ ሳይሆኑ፣ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን የሚያበረክቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሰላም፣ የእርቅና የአንድነት መገለጫ የሆነው የዲዚ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ከይ ቢያርግ” በዓል በማልማትና በመጠበቅ ለክልላዊ አንድነት መጠቀም እንዳለበት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተዋል።

በበዓሉ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር  አማካሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በከይ ቢያርግ በዓል የታየውን ህዝባዊ አንድነት ለአካባቢና ለክልላዊ ሰላምና ልማት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ ከይ ቢያርግ የሚያስተምረን እርቅ ሰላምና ምርታማነትን ሲሆን  ይህንን እሴት በመጠቀም ወደ ላቀ ልማትና ብልጽግና ለመሸጋገር በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል ።

የማጂ ከተማ ከንቲባ አቶ እሸቱ አየለ በበኩላቸው የዲዚ ብሔረሰብ የስልጣኔ፣ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።

የብሔረሰቡ ምሁራን ተወላጆች ባህሉ መሠረታዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ በጥናትና ምርምር ማዳበር፣ ማልማትና ለማስተዋወቅ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የዲዚ ምሁራን ጥናትና ምርምር የበላይ ጠባቂ አቶ መቱ አኩ በበኩላቸው በዓሉ ከክረምቱ ጭጋግ ወደ ብሩህ ፀሐይ፣ ከአሮጌ ዘመን ወደ አዲስ ዓመት የሚደረግ ሽግግርን የሚያመለክት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ጽኑ ማሳያ ነው ብለዋል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።