December 25, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል

ማሻ፣ ታህሳስ 16/2018 (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የዘንድሮው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል “ስፖርት ብዝሃነትና እወቀት ለልህቀት” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 9 እስከ 24 በጅማ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል፡፡

በፌስቲቫሉ በሁለቱም ጾታ በ15 የስፖርት አይነቶች ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን፥ የስታዲየም፣ የመዋኛ ገንዳ እድሳትን ጨምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ሁነቱ ከስፖርታዊ ውድድሮች ባሻገር ባህልን ለማስተዋወቅና የእርስ በእርስ አብሮነትን ለማጠናከር እድል ይፈጥራል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን፥ ሁሉንም የስፖርት መወዳደሪያ ስፍራዎች በማዘጋጀት ውድድሩ በድምቀት እንዲከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለውድድሩ ራሱን የቻለ ድረገጽና የሞባይል መተግበሪያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁን በበኩላቸው፥ ከስፖርታዊ ውድድሮች ጎን ለጎን የባህል ልውውጥና የኪነ ጥብበ ዝግጅቶች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

#ኤፍ ኤም ሲ