ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረሃይል ምክክር መድረክ ተጠናቀቀ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጋራ ትብብር ዠ ባዘጋጀው በዚሁ መድረክ ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንዲሁም ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር አደረጃጀት ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርበው ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ለኑሮ ውድነት መባባስና ለክልላዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ ከመሆን ባሻገር ለጸጥታው ጭምር ሥጋት ነው።
የክልሉ መንግስት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመግታት በኃላፊነት እንደሚሰራ ነው ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የተናገሩት።
ጤናማ ያልሆነ የንግድ ሥርዓት እና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ኑሮ ውድነትን ከማባባስ ባሻገር ለገቢ አሰባሰብ ሂደቱ እንቅፋት በመሆኑ በየደረጃው ካላቸው የንግድ ተቋማትና ጸጥታ መዋቅሮች ጋር በተቀናጀ መሠራት እንደሚገባም አንስተዋል።
በክልሉ ያለአግባቡ የተበራከቱ ኬላዎች እንዲነሱ መንግስት አቅጣጫ በማስቀመጥ እንዲነሳ ያደረገ ቢሆንም አሁንም መልኩን ቀይሮ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋለ በመሆኑ በዚህ ላይ በልዩ ትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በማደያዎች ፍትሃዊ የነዳጅ ምርት አቅርቦትና ሥርጭት እንዲኖር መሠራት አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የነዳጅና ሌሎች ፎጆታ ምርቶችን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩና ግብይት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ እርምጃ የመውሰዱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
በህገወጥ መንገድ የተበራከቱ የነዳጅ ማዳያ ግንባታዎችን ማስቆምና በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ከማረም ባሻገር በአንዳንድ አከባቢዎች የነዳጅ ማደያ እጥረት ለመቅረፍ ይሰራልም ብለዋል።
በክልሉ ህገወጥ ንግድ፣ ዋጋ ንረት እንዲሁም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት በየደረጃው ሥራዎች በልዩ ትኩረት መምራትና መከታተል እንደሚያስፈልግም ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
ፍትሃዊና ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ግብረሃይሉን በማጠናከር ተከታታይ መድረኮችን እያካሄደ መሄድ አስፈላጊ እንደሆነ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ገልጸዋል።
የክልሉ አመራር ህገወጥ ንግድ፣ ዋጋ ንረትና ህገወጥ ኬላዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በልዩ ትኩረት እንዲከታተል እና እንዲመራም አቶ ፍቅሬ አማን አስገንዝበዋል።
በክልሉ በህገወጥ መንገድ የፍጆታ ምርቶች የሚያከማቹ፣ ምርት የሚያዘዋውሩ እና ያለ ንግድ ፍቃድ ግብይት የሚፈጽሙ ተቋማትና አካላትን የመቆጣጠሩ ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ናቸው።
ኑሮ ውድነት የሚያረጋጉ ሰንበት ገበያዎችን በማስፋፋት ደረጃቸውን የጠበቁ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ይሰራል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ጤናማ የንግድ ግብይት ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ ይሰራልም ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የግብረሃይል አባላት በቡና፣ በወርቅ ምርቶችና በሌሎች ማዕድን ሀብቶች እንዲሁም ፍጆታ እቃዎች ያለ ህጋዊ ንግድ ፍቃድ ግብይት የሚፈጽሙና ዝውውር የሚያደርጉ አካላት እየተበራከቱ መሆናቸውም ተናግረዋል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።
More Stories
የገና በዓል አከባበር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች…
ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቀ
ፕሬዚዳንት ታዬ ለፈረንጆች የገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ