December 25, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሚዲያዎች ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎችን ተደራሽ እያደረጉ መምጣቸውን ተከትሎ እየተመዘገ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራርን መዘርጋት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑ ተመላከተ።

በዶክተር ወልደማርያም በዛብህ የተመራው የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባለሙያዎች የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትና የሸካ ማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥንን የስራ እንቅስቃሴ ላይ መክሯል።

ማሻ፣ ታህሳስ 15/2018 (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የሀገርን ገጽታ በመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን በጽኑ መሠረት ላይ ከመገንባት አንጻር የመገናኛ ብዙኀን አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ይታመናል።

መንግስት ለሚዲያው ዘርፍ የሰጠውን ነጻነት በመንተራስ በብሮድካስት አዋጅ ፍቃድ አግኝተው የተደራጁ የህዝብና የመንግስት ሚዲያዎች የኤዲቶሪያል አሰራርን ተንተርሰው መስራት እንዳለባቸውም ይታመናል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ  ምክትልና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ወልደማርያም በዛብህ እንደ ሀገር የተያዘውን የለውጥ ጉዞ ከመደገፍና ከማስረጽ አንጻር ሚዲያ ያለውን እምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ከተቋቋሙ አጭር ጊዜ ያስቆጠሩት የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እና የሸካ ማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅቶች በመረጃ ስርጭት ረገድ እያከናወኑት ያለው ስራ ለክልሉ ነባር ሚዲያዎች አርአያ መሆኑንም አመላክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሚዲያዎችን ደጀን በማድረግ አካባቢያዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ ስነ ምድርና ከርሰምድር ሀብቶችን ለማስተዋወቅ የተናበበ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ዶክተር ወልደማርያም አብራርተዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ  ምክትል ስራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ  ታደሰ ጋረፎ በተቋሙ እቅድ፣ አጀንዳ ቀረጻና የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ያለውን አፈጻጸም በሰፊዉ አብራርተዋል።

ወቅቱ የማህበራዊ ሚዲያ  በጎና አሉታዊ ተጽዕኖ የሚጎላበት የመሆኑን ያህል ለህዝቡና ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮችን በመለየት መስራት የዜግነት ግዴታ ጭምር መሆን በክልል ኮሙኒኬሽን  የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ የሚዲያ ይዘት ማበልጸግና ስርጭት ዳይሬክቶረት  ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ግርማ አመላክተዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል ብርታት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።